በበጀት ዓመቱ ከ2 ሺህ ቶን ቡና በላይ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 02/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጎፋ ዞን በተያዘው በጀት ዓመት 2 ሺህ 200 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱ ተገለጸ።

የዞኑ ግብርና መምሪያ የበጋ መስኖ የቡና ልማት እና የሲንክሮናይዜሽን ዞናዊ የንቅናቄ መድረክ አካሄዷል።

የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ተወካይ እና ምክትል ኃላፊና የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙሉቀን ተመስገን የአርሶአደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የወተትና የወተት ወጤቶች አቅርቦት ከፍ ለማድረግ የተሻሻለ ዝሪያ ያላቸውን ከብቶች ለማርባት በዝሪያ ማሻሻያ ፕሮግራም አርሶአደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዞኑ 298 የወተት መንደር መደራጀቱን ገልጸው የመኖ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት በቅንጅት እንደሚሰራ ተመላክቷል።

የዞኑ ቡናና ቅመማ ቅመም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኑርአዲስ አደም በበኩላቸው በያዝነው የበጀት ዓመት የቡና ምርታማነትና ጥራት ላይ በትኩረት በመስራት 2 ሺህ 200 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለመላክ  ስለመታቀዱ አብራርተዋል።

በዞኑ ከ24 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በቡና መሸፈኑን ገልጸው በሄክታር ቀደም ሲል አምስት ኩንታል ከሚመረትበት በአሁን ወቅት ወደ ሰባት ነጥብ ሁለት ኩንታል በሄክታር ማምረት መቻሉን ገልጸዋል።

በመምሪያው የአዝርዕት ሰብሎች ልማት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ጊታ የውሃ አማራጮችን በአግባቡ በመጠቀም በበጋ ወራት ከ14 ሺህ ሄክተር በላይ በማልማት ከ3 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ስለመታቀዱ አንስተዋል።

25ሺህ ኩንታል ስንዴ በበጋ ወራት ለማምረት ዝግጅት መደረጉን አቶ ተስፋዬ አንስተዋል።

የጎፋ ዞን መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ታደለ ያዕቆብ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና አቅርቦት ችግሮችን በመፍታትና ምርትና ምርታማነት በመጨመር “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት” ለመሸጋገር የሚደረገው እንቅስቃሴ ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በግብርናው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት የአርሶአደሩን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን