ሀዋሳ፡ ጥቅምት 01/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በመኸር እርሻ ባለሙት የስንዴ ማሳ ላይ የዋግ በሽታ በመከሰቱ አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው የማሪ ማንሳና ቶጫ ወረዳ አርሶ አደሮች ጠይቀዋል።
የሰብል በሽታ አሰሳ በማድረግ አስፈላጊው ፀረ-ተባይ ለማስገባት እየሰራ እንደሚገኝ የዳውሮ ዞን ግብርና፣ አካበቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ መምሪያ አስታውቋል።
በዘንድሮ መኸር እርሻ የተሻለ ምርት ለማግኘት አልመው በግብርናው ምክረሃሳብ መሠረት ምርጥ ዘር ስንዴ በሙሉ ቴክኖሎጂ መዝራታቸውን የማሪ ማንሳ ወረዳ አርሶአደር በዛብህ በተላ እና አለማየሁ ግንባቶ ተናግረዋል።
ከአቻዎች ጋር ተደራጅተው በግለሰብ ማሳ በጋራ ለማምረት በማሰብ 2 ኩንታል ምርጥ ዘር ገዝተው በመኸር እርሻ ስራ ላይ መሣተፋቸውን የሚገልጹት ደግሞ ወጣት በረከት ኃይሌ እና ታደሰ አመለ ናቸው፡፡
የተሻለ ምርት ለማግኘት ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን ያፈሰሱ ቢሆንም በስንዴ ማሳቸው የገባው የዋግ በሽታ ስጋት እንደደቀነባቸው ገልፀዋል።
የሚመለከታቸው አካላት በሰብሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሳይደርስ አስፈላጊውን ፀረ-ተባይ መከላከያ እንዲያቀርብላቸው ጠይቀዋል።
የዕድገት ቀበሌ ግብርና ባለሙያ ካሳሁን ኃይለሚካኤል የሰብል በሽታ አሰሳ በማድረግ ተባይ በተከሰተባቸው ማሳዎች ፀረተባይ ለመርጨት መዘጋጀታቸውን በመጠቆም የስንዴ ዋግ በሽታ ፀረተባይ ግን በገበያ ዋጋው ውድ በመሆኑ ለሚመለከተው አካል አሳውቀናል ብለዋል።
የማሪ ማንሳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተካልኝ በቀለ በበኩላቸው በእርሻ ወቅት ሁሉም መልማት የሚችል መሬት በምርት እንዲሸፈን በትኩረት መሰራቱን ገልፀዋል። ከስንዴ ፀረተባይ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የዳውሮ ዞን ግብርና፣ አካበቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ መምሪያ ኃላፊ ተወካይ አቶ ዋታላ ዋጄ በዘንድሮው መኸር እርሻ ከ 79 ሺህ 119 ሄክታር መሬት ታርሶ በዘር መሸፈኑን ገልጸው፥ ከዚህም ከ1 ሚሊየን 484 ሺህ በላይ ኳንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ጠቁመዋል።
የስንዴ ዋግ በሽታን በሚመለከትም የሰብል አሰሳ ከዞን በወረዱትና በየደረጃው ባሉ ባለሙያዎች እየተደረገ እንዳለ ተናግረው፥ ፀረ-ተባይ ለማቅረብም ከክልል አካላት ጋር እየሠራን እንገኛለን ሲሉ የመምሪያው ተወካይ አስታውቀዋል።
ዘጋቢ፡ ዮሐንስ መካሻ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ