ኮሌጁ ከመንግስት በጀት ድጐማ ነፃ ሆኖ መስራት እንዲችል የራሱ የገቢ ማስገኛ ስራዎች በስፋት እየሰራሁ ነው – የሚዛን ግብርና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ

ሀዋሳ፡ መስከረም 30/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ኮሌጁ ከመንግስት በጀት ድጐማ ነፃ ሆኖ መስራት እንዲችል የራሱ የገቢ ማስገኛ ስራዎች በስፋት እየሰራ መሆኑን የሚዛን ግብርና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ አስታወቀ፡፡

ኮሌጁ በአሁን ጊዜ 2ሺህ የእንቁላል ዶሮ በማርባት በቀን ከ1200 በላይ እንቁላል ለገበያ እያቀረበ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

በኮሌጁ የኢንተርኘራይዝ ስራ አስኪያጅ መ/ር ዋለልኝ አለምነህ በፌደራል ስራና ክህሎት ሚኒስቴር ስር ከሚገኙት አምስት የግብርና ኮጆች አንዱ የሆነው የሚዛን ግብርና ኮሌጅ በስራና ክህሎት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ከመንግስት በጀት ድጐማ ነፃ ሆኖ መስራት እንዲችል የራሱ ገቢ ማስገኛ ሰራ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በዚህ መሠረትም በ2016/17 በጀት ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ ሁለት ሺህ የእንቁላል ዶሮ በማስገባት እንቁላል ማምረት መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡

በኮሌጁ ደረጃ አስር ሺህ ዶሮ ለማርባት ዕቅድ የተያዘ መሆኑን መ/ር ዋለልኝ ጠቁመው በ2017 በጀት ዓመት እስከ ሰባት ሺህ የእንቁላል ዶሮ ለማስገባት ተጨማሪ ግንባታ ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን አብራርተዋል፡፡

ዶሮዎቹ አሁን ላይ እድሜያቸው ስድስት ወራት እየተጠጋ እነደሆነ የገለፁት ስራ አስኪያጁ በአንድ ቀን እስከ 1200 እንቁላለ መሰብሰብ እየቻልን ነው ብለዋል፡፡

ከእንቁላል ዶሮ እርባታ ባለፈ 26 የወተት ላሞችን ማርባት የሚያስችል ቤት ለመገንባት ቁሳቁስ ተዘጋጅቷልም ብለዋል፡፡

ከንብ ማነብም ማር ለማምረትም 250 ዘመናዊ ቀፎ ተዘጋጅቶ ስራ መጀመሩንም አክለው ገልፀዋል፡፡

በኮሌጁ የእንስሳት ት/ት ክፍል መምህርና የዶሮዎች ሱፐርቫይዘር መ/ር ሙርቴሳ ለገሠ በበኩላቸው የኮሌጁ ግቢ ለዶሮ እርባታ ምቹ መሆኑን ገልፀው የዶሮዎቹ ጤንነት አስተማማኝ እንዲሆን ቀን በቀን ክትትል እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡

የዶሮዎቹንና የዶሮ ቤት ሙቀት ለመቆጣጠርም ዘመናዊ የሙቀት መቆጣጠሪያ መሣሪያ ተገጥሞ ክትትል እንደሚያደርጉ አስረድተዋል፡፡

ሌላው በኮሌጁ የእንስሳት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት መምህር ዱጋሣ ኦሊቃ በበኩላቸው ከዶሮዎቹ ጥራት ያለው እንቁላል ለማግኘት አረንጓዴ ተክሎች እንደ ጐመን ያሉትን በማቅረብ በአካባቢው ተፈላጊ የሆነውን የእንቁላሉ ቢጫ ክፍል የበዛበት እንቁላል እያመረቱ ለኮሌጁና ለአካባቢ ማህበረሰብ እየሸጡ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ወሰኑ ወዳጆ – ከሚዛን ጣቢያችን