ከፍታ ማይክሮ ፋይናንስ ሆሳዕና ቅርንጫፍ ከዲጆ ኢንተርፕራይዝ ጋር በመሆን የጫማ ውበትና ጽዳት ዙሪያ ያዘጋጀው ስልጠና ነክ የውይይት መድረክ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።
የከፍታ ማይክሮ ፋይናንስ ሆሳዕና ቅርንጫፍ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ኡሎሮ፤ ወጣቶች በየትኛውም የስራ መስኮች ተሰማርተው ለሀገር የጋራ ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡ በቅንጅት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
ከፍታ ማይክሮ ፋይናንስ ለንግድ ስራ መስኮች የብድር ገንዘብ በማቅረብ፣ የቁጠባ አገልግሎት በመስጠትና ሌሎች ተዛማጅ ስራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኝ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም መሆኑን የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ፤ ተቋሙ ከመንግስት ባለድርሻ አካላትና አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ስራ ፈጣሪ ወጣቶች የቁጠባን ባህል በማዳበር የነገን ሕይወት ለማሻሻል ከጥቂት መነሻ ተነስተው ለተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ ለማድረግ የሚሰራ እንደሆነ አመላክተዋል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት የስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተመስገን ወርቁ በበኩላቸው በጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ስራ መስኮች ለተሰማሩና በከተማም ሆነ በገጠር ስራ ፈጣሪ ለሆኑ ወጣቶች ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ለሀገር ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ስልጠናው ስራ ፈጣሪ ወጣቶቹ ለከተማው ውበትና ጽዳት የድርሻቸውን እንዲወጡ ግንዛቤ የሚፈጥር መሆኑን በመጠቆም ይህም በከተማው እየተሰራ ለሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ አጋዥ መሆኑን አንስተዋል።
በዕለቱ ለስራ ፈጠሪ ወጣቶቹ ስልጠናውን የሰጠው የ”ባለታንከሯ ሊስትሮ” ባለቤትና ስራ ፈጣሪ ወጣት ሙሃባ ረዲ፤ ወጣቶች ስራ ሳይንቁ መስራት ለነገ የተሻለ ሕይወት መሰረት መሆኑን ጠቁሞ የስራ ባህልን በማዳበር ወጣቶች ነጋቸውን የተሻለ ለማድረግ ከወዲሁ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁሟል።
ስልጠናው “የዛሬው ሊስትሮ ጠንክሮ ሰርቶ ነገ ካሰበበት ይደርሳል” በሚል መሪ ቃል የተካሄደ ሲሆን በሆሳዕና ከተማ የሊስትሮ ሠራተኞች የሆኑ የስልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡን አስተያየት በሚሰሩት የሊስትሮ ስራ ከራሳቸው አልፎ ቤተሰቦቻቸውን እያገዙ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
ባገኙት ስልጠና መሰረት ቁጠባን ባህል ለማድረግ ግንዛቤ ማግኘታቸውን የጠቆሙት ወጣቶቹ ሌሎችም ወጣቶች ጊዜያቸውን በአልባሌ ስፍራዎች ከማሳለፍ ይልቅ ማንኛውንም ስራ ፈጥሮ መስራት ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ