በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል የትምህርት ግብኣት አለመሟላት ችግሮች ሊፈቱ እንደሚገባ በዳውሮ ዞን የታርጫ እና ማሪ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጠይቀዋል

የትምህርት ግብኣት ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ አሠራሮችን ዘርግቶ እየሠራ እንደሚገኝ የዳውሮ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታውቋል።

ተማሪዎች በክረምት እረፍት ጊዜያቸው ለቀጣዩ ክፍል አጋዥ የሆኑ ዝግጅቶችን እያደረጉ ቆይተው አሁን ላይ የትምህርት ዘመኑን መማር በጥሩ ሁኔታ እየቀጠሉ እንደሆነ በታርጫ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ዳግም ዓለሙ፣ ዘፀኣት ጎሳሎ እና ኢዮብ ይስሃቅ ገልፀዋል።

የማሪ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እፀገነት አብረሃም፣ ዝናው ተረፈ እና ሠርካለም አባቴ በበኩላቸው የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የአዳር እና ከትምህርት ሰዓት ውጪ ጥናት እንዲያደርጉ በትምህርት ቤቱ እንደተመቻቸላቸው አንስተዋል።

ለተሻለ ውጤት የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረው ለዚሁም በቡድን ማጥናትና የኢንተርኔት ቴክኖሎጂም እየተጠቀሙ እንዳለም ተማሪዎቹ ተናግረዋል።

ለትምህርት ውጤታማነት አስፈላጊ የሆኑ  የመጽሐፍት እጥረት፣  ላቦራቶሪ አገልግሎት አለመሟላትና በመምህራን ደመወዝ መዘግየት ምክንያት የሚከሰት የትምህርት ብክነት ችግሮች እንዲፈቱም ጠይቀዋል።

ለዘንድሮው የትምህርት ዘመን አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ማስተማር መጀመራቸውን የሚገልጹት መምህር ተመስገን መሸሻ፣ መምህር ዳግም ዳንኤል እና መምህር ዘነበ ምትኩ ውጤታማ ተማሪን ለማፍራት ከትምህርት ጊዜ ባለፈ የሜካፕ ጊዜንም ተጠቅመው እያስተማሩ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

በ2016 ትምህርት ዘመን 12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱት ተማሪዎች መካከል ከሁለቱም ትምህርት ቤቶች እያንዳንዳቸው ስምንት እና በድምሩ 16 ተማሪዎች ለዩኒቨርስቲ የሚያበቃ ውጤት ማምጣታቸውን ርዕሰ መምህራን አቶ ታደለ ተፈራ እና አቶ መኩሪያ ማጆር ተናግረዋል።

ውጤቱ ከአምናው አንፃር ሲታይ መሻሻል የታየበት ቢሆንም የተማሪ ውጤት ይበልጥ ለማሳደግ እየተሠራበት ነው ሲሉም ርዕሰ መምህራኑ ገልፀዋል።

የትምህርት ብክነትን እያስከተለ እንዳለ የተጠቀሰው የመምህራን ደመወዝ መዘግየትን ለመፍታትና የትምህርት ውጤታማነትን ለማሳደግ ወረዳው የበኩሉን ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ የማሪ ማንሳ ወረዳ ዋና አስተዳደር አቶ ተካልኝ ተናግረዋል።

የዳውሮ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደለ ታዬ በበኩላቸው በ2017 የትምህርት ዘመን ከዞኑ ሰማኒያ ስምንት ተማሪዎች የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት ማምጣታቸውን ተናግረው ይኸውም ከአምናው አንፃር በእጥፍ የጨመረበት መሆኑን አንስተዋል።

ለዚሁም ትምህርት ቤቶቹ ማህበረሰቡን በማስተባበር የተለያዩ ሁኔቶችን በማመቻቸት የአዳርና ሌሎች የጥናት መርሃግብር ማዘጋጀታቸውን ጨምሮ የመምህራን እና የተማሪዎች ጥረት ተጨምሮ የመጣ መሻሻል እንደሆነ ጠቅሰዋል

የትምህርት ግብኣት እጥረቶችን ለመፍታት ከፌደራል የደረሱ የመማሪያ መጽሐፍቶች ለየትምህርት ቤቶች እየተዳረሱ እንደሆኑና ለቤተሙከራ አገልግሎትም ግብኣት ለሟሟላት ለየትምህርት ቤቶች የውስጥ ገቢያቸውን ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛሉ ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ዮሐንስ መካሻ – ከዋካ ጣቢያችን