በክልሉ የፕላን ትግባራ ወቅት የከተሞችን መዋቅራዊ ፕላን በማዘጋጀት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ
የሆሳዕና ከተማ ለቀጣይ 10 ዓመታት ተግባራዊ በሚደረገው መዋቅራዊ ፕላን ላይ የማጠቃለያ ውይይት የተለያዩ የህብረተሰብ ተወካዮች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
በምክክር መድረኩ አዲስ በተዘጋጀው የሆሳዕና ከተማ መዋቅራዊ ፕላን ላይ በመሬት አጠቃቀም እና ሶሺዮ ኢኮኖሚክ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች ለውይይቱ ተሳታፊዎቹ የቀረቡ ሲሆን የመድረኩ ተሳታፊዎችም አዲስ የተዘጋጀው መዋቅራዊ ፕላን የከተማውን ሁለንተናዊ ልማትን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በከተማው በፕላኑ መሠረት ለኢንቨስትመንት፣ ለአርንጓዴ ልማትና ለሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ይውላሉ የተባሉ አካባቢዎች በአዲሱ መዋቅረዊ ፕላን ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ የአገልግሎቶች ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ ደፋር እንዳሉት፤ በከተማው ላለፉት 10 ዓመታት ሲተገበር የነበረው ፕላን በ2014 ዓ.ም ጊዜው ማብቃቱን ተከትሎ አዲስ መዋቅራዊ ፕላን መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
አዲሱ የሆሣዕና ከተማ መዋቅራዊ ፕላን 7 ሺህ 391 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ በፕላኑ ዙሪያም በየደረጃው ከህዝብ ጋር ሰፊ ውይይቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳዊት ጡምደዶ በበኩላቸው በአዲሱ ፕላን የማህበራዊ አገልግሎቶች የህዝብ መናፈሻዎች እና ለሌሎች አገልገሎቶች የሚዉሉ ቦታዎችና የህዝቡ የዘመናት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ተደርጎ መሰራቱን ገልጸዋል።
የፕላን ትግበራ ከከተማ ገቢ ጋር የተቆራኘ በመሆኑን ፕላኑን ወደታች በማውረድ ለህዝቡ ልማትን ለማምጣት ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ ወሳኝ መሆኑንም ከንቲባው አንስተዋል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ፕላኑን በከተማ ምክር ቤት በማጽደቅ ወደ ትግበራ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ እንደገለጹት በአዲሱ መዋቅር ፕላን አተገባበር ላይ ከህዝብ ጋር በቂ ውይይቶችን ማካሄድ በመቻሉ የተሻሉ ስራዎች መሠራታቸውንና በሂደት የሚሻሻሉ ነገሮች እየተሻሻሉ እንደሚሄዱ ተናግረዋል።
ፕላኑም የሆሣዕና ከተማን የዘመናት የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያግዝ እና ሆሳዕና ከተማን ከሌሞ ወረዳ ጋር በመሰረተ ልማት የሚያስተሳሰር እንዲሁም በርካታ የስራ ዕድሎችን የሚፈጥር መሆኑንም ዋና አስተዳዳሪዉ ጠቅሰዋል።
በኢንቨስትመንት ስም መሬት ወስደው ያላለሙ ግለሰቦች መሬቱን ለመንግስት እንዲመልሱ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በተለይ በሆሳዕና ከተማ ዙሪያ የሚገኙ የሌሞ ወረዳ አርሶአደሮች መሬታቸውን በአግባቡ መያዝ እንዳለባቸዉም አሳስበዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ በምክትል ቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የከተማ ፕላን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ አየለ በበኩላቸው የሆሳዕና ከተማ የቀጣይ 10 ዓመታት መዋቅራዊ ፕላን ዝግጅት የተሳካ እንዲሆን የጋራ ርብርብ ማድረጋቸውን ጠቅሰዉ ፕላኑም ለከተማዉና ለአጎራባች ወረዳዎች መልካም ዕድሎችን የሚያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ በ2016 በጀት ዓመት 61 የተለያዩ ፕላኖች መዘጋጀታቸውን የገለጹት አቶ አባይነህ በተያዘዉ በጀት ዓመትም የፕላን ትግበራ ወቅት ያለፈባቸውን በክልሉ የሚገኙ ከተሞችን መዋቅራዊ ፕላን የማዘጋጀት ስራ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በመድረኩም የፌደራል፣ የክልል፣ የሀዲያ ዞን የሆሳዕና ከተማና የሌሞ ወረዳ አመራሮች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የምሁራን፣ የወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡ ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ