የሆሣዕና ከተማ አስተዳደር በቀጣይ ለ10 ዓመታት በሚተገበረው መዋቅራዊ ፕላን ዙሪያ ከባለድርሻ አካለት ጋር የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

ሀዋሳ፡ መስከረም 27/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሆሣዕና ከተማ አስተዳደር በቀጣይ ለ10 ዓመታት በሚተገበረው መዋቅራዊ ፕላን ዙሪያ ከባለድርሻ አካለት ጋር የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ ደፋር እንዳሉት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 10 ዓመታት ሲተገበር ከነበረው ፕላን መልካም ተሞክሮዎችን በመዉሰድ የከተማዋን የቀጣይ 10  ዓመታት መዋቅራዊ ፕላን ማዘጋጀት መቻሉን አንስተዋል።

የከተማ ፕላን በዋናነት ህዝቡን የሚጠቅም ከህዝብ ለህዝብ ነዉ ያሉት አቶ ደሳለኝ በእስካሁኑ ሂደት አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

የፕላኑ ዝግጅት የከተማዋን ሁለንተናዊ ዕድገት ያፋጥናል ተብሎ የሚጠበቅ ስሆን  የፕላኑ ዝግጅት ላይም በየደረጃው ምክክሮች መደረጋቸውን ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ የመሬት አጠቃቀም እና socio- economic ላይ የተደረጉ ጥናቶች እየቀረበ የሚገኝ ሲሆን ከተሳታፊዎች ገንቢ አስተያየቶች ይወሰዳል ተብሎ ይጠበቃል።

በመድረኩም የከተማና መሰረተ ልማት  ሚኒስትር  የከተማ ፕላን ዝግጅት ዴስክ ኃላፊ አቶ አባይነህ አጎናፍር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ በምክትል ቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የከተማ ፕላን ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ አየለ የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዎስ አኒዮ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደዊት ጡሚደዶ የክልል የዞን የሆሳዕና ከተማ አመራሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ዘጋቢ፡ ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን