የቶጫ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ መስከረም 27/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቶጫ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለተሻለ ህክምና ፍለጋ ወደ ሌሎች አከባቢ የሚደርጉ ጉዞዎችን ለማስቀረት የሚያስችል አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ከዚህ ቀደም የተሻለ ህክምና ፍለጋ ወደሌሎች አካባቢ የሚደረጉ ጉዞዎችን በማስቀረትና አገልግሎቶችን በቅርበት ማግኘታቸው ከከፍተኛ ወጪ እየታደጋቸው እንደሚገኝ የሆሲፒታሉ ተገልጋዮች ተናግረዋል፡፡

በ4ቱ ወረዳዎች ለሚገኙ ከ4 መቶ ሺህ በላይ ዜጎች አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የቶጫ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፥ ከዚህ ቀደም በሆስፒታሉ ያልነበሩ የጠቅላላ ቀዶ ጥገናና የእናቶች ቀዶ ማዋለድ ህክምናዎችን በዘርፉ ባለሙያዎች እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ካነጋገርናቸው ተገልጋዮች መካከል አቶ ተሰማ በገጆ እና መምህርት አስቴር ታደለ ልጆቻቸውን ለማሳከም መምጣታቸውን መቁመው በሆስፒታሉ እየተሰጡ ያሉ አገልግሎቶች ከዚህ ቀደም ወደ ታርጫ፣ ጅማና ወላይታ በመሄድ የሚያወጡትን ጊዜ፣ ጉልበትና የኢኮኖሚ ወጪ በአቅራቢያቸው ማግኘት መቻላቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡

አቶ አክሊሉ ተፈራ እና ደለለኝ ቤሩ ደግሞ ከአጎራባች ወረዳ አካባቢዎች ለህክምና አገልግሎት መምጣታቸውን ተናግረው በተለይም በእናቶችና ቀዶ ጥገና የህክምና ዘርፎች እየተሰጠ ያለው አገልግሎት በቅርበት ማግኘታቸው ገልጸዋል፡፡

በሆስፒታሉ በርካታ ተገልጋይ ያለበት እንደሆነና የተቋሙ ባለሙያዎች ለሁሉም ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት የሚያደርጉት ርብርብ የሚያስመሰግን እንደሆነ ገልፀው፥ በቀጣይነት የሚስተዋለውን የመድሃኒት እጥረት እንዲፈታ ጠይቀዋል፡፡

የመድሃኒት አቅርቦቱ እጥረት እንዳለ የሚናገሩት የሆስፒታሉ መድኃኒት ክፍል አስተባባሪ አቶ አማኑኤል አማንቾ እስሁን አቅርቦቱ 30 በመቶ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የሆስፒታሉ ስራአስኪያጅ አቶ ውበቴ ኡቴ እንደሚገልፁት በሆሲፒታሉ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ይበልጥ ለማሳደግ 2 ስፔሻሊስት ባለሙያዎችን ጨምሮ ሌሎችንም በማሟላት አሁን ላይ የእናቶችና የጠቅላላ ቀዶ ጥገና ህክምና አገልግሎቶች ማቅረብ መቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተቋሙ የሚስተዋሉ የተለያዩ መገልገያ መሣሪያ እጥረቶችን ለማሟላትም በማህበራዊ ሚዲያ ንቅናቄ በመፍጠር 2 መቶ ሺህ የሚገመት ገቢ በማሰባሰብ ፍራሽ፣ አንሶላና አልጋ ለማሟላት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የተሻለ የህክምና አገልግሎቶችን ለመስጠት እንዲቻልም ባለሙያ ትርፍ ጊዜ ክፍያ እና የመድኃኒት እጥረት ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ ውበቴ ገልፀዋል፡፡ 

ዘጋቢ፡ ዮሐንስ መካሻ – ከዋካ ጣቢያችን