በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የሚባክነውን የህዝብና የመንግሥት ሀብት ማዳን መቻሉ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 26/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በህገ ወጥ ቅጥሮችና በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የሚባክነውን የህዝብና የመንግሥት ሀብት ማዳን መቻሉን የጌዴኦ ዞን ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት መምሪያ አስታወቀ።

የ2016 ሥራ አፈፃፀም ግምገማና 2017 ዓ/ም መሪ ዕቅድ በማውረድ የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ መዋቀሮች እውቅና የመስጠት መርሀግብር ተካሂዷል፡፡

የመምሪያውን የ2016 በጀት ዓመት የአፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት በመምሪያው የልማት ዕቅድ ቡድን መሪ አስተባባሪ ተወካይ አቶ መኮንን ጪጩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመደበኛ ሥራ 993 ትምህርት ማስረጃዎችን ለመፈተሽ ከተለዩት ውስጥ 55 ሀሰተኛ የትምህርት መረጃዎችን ማረጋገጡ ተናግረዋል፡፡

በዞኑ የተከናወኑ 2 ሺህ 952 ቅጥር፣ ደረጃ ዕድገትና ዝውውር ውስጥ 61 የሚሆነው ቅጥር ህገ ወጥ በመሆኑ መሰረዙን ጠቁመው፥ በአጠቃላይ ከመንግሥት ካዝና ይወጣ የነበረውን 1 ሚሊዮን 220 ሺህ ብር ማዳን እንደተቻለ ተወካዩ አብራርተዋል፡፡

መምሪያው 7 ሺህ 852 የትምህርት መረጃዎችን ለመሰብሰብ ካቀደው እስከ አሁን 5 ሺህ 456 መሰብሰቡንና የማጣራቱን ሥራ በፌዴራል መንግሥት የሚከናወን እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የዞኑ ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታምራት ደልቦ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ከባለሙያ ጀምሮ እስከ ሴክተር ድረስ የተከናወኑ ሥራዎችን በመከታተል፣ ጠንካራ ፐብሊክ ሰርቪስ ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተገልጋዮችን እርካታ ከማሳደግ አንጻር የተለዩ  ውስንነቶችን ለመቅረፍ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የሰው ሀብት ልማት አመራር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዘሪሁን ማሞ በሰው ሀብት መረጃ አያያዝና አደረጃጀት፣ የተገልጋዮች እርካታ ዳሰሳና በሌሎች ጉዳዮች በተደጋጋሚ የሚነሱ የአፈፃፀም ጉድለቶች በመቅረፍ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት በመስጠት የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

መምሪያውና ሌሎች ባለድርሻዎች መፈታት እየተቻለ ሳይፈቱ የሪፖርት አካላት ብቻ ሆነው የሚመላለሱ ጉዳዮችን ለይቶ መፍታት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ዘርሁን ሠራተኞች የመንግሥት የሥራ ሰዓት በአግባቡ በማክበር ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

መድረኩን የመሩት የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ረዳት የመንግሥት ተጠሪና የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ምህረቱ ተፈሪ  ተገልጋዮች ከኪራይ ሰብሳቢነት የፀዳ አገለግሎት እንዲያገኙ በማድረግና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ በአፈፃፀም የሚታዩ ውስንነቶችን በመፍታት ለተሻለ ውጤት በቁርጠኝነት መረባረብ አስፈላጊ እንደሆነ አቶ ምህረቱ ገልፀዋል፡፡

በሁሉም መዋቅሮች የተሻለ በመፈፀም ፊት ለወጡ ሠራተኞችና ተቋማት እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል፡፡

ዘጋቢ፡ እምነት ሽፈራው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን