የ”ጎፋ ጋዜ ማስቃላ” ማጠቃለያ የሆነው “ጊያ ካንሶ” (ገበያ ማቋረጥ) ባህላዊ ክብረ በዓል በጎፋ ዞን ዛላ ወረዳ በድምቀት ተከብሯል

የዛላ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ጨንቻ የወረዳው ልዩ መገለጫ የሆነው ገበያን የማቋረጥ ወይም በአካባቢው መጠሪያ “ጊያ ካንሶ” አዳዲስ ሙሽሮች ደምቀው ገበያ የሚወጡበት፣ ልጃገረዶችና ጎረምሳዎች የሚተያዩበትና መፈላለጋቸውን በመግለጽ የሚተጫጩበት በዓል መሆኑን አስረድተዋል።

የፈረስና በቅሎ ግልቢያ የሚከናወንበት፣ አዲስ የተሾሙ “እራሻዎች፣ ቢታንተዎች እና ሁዱጋዎች” ተብለው የሚጠሩ ባህላዊ መሪዎች ለህዝቡ የሚተዋወቁበት በዓል ስለመሆኑም አቶ ግርማ አብራርተዋል።

በበዓሉ ህዝቡ ባህላዊ ጭፈራ እየጨፈሩ ገበያውን ሦስት ዙር የሚያቋርጡበትና አዲሱ ዓመት የሠላም፣ የፍቅር፣ የበረከትና የወንድማማችነት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን የሚገልጹበት መሆኑን ጠቁመዋል።

የዛላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ያዕቆብ ዘካሪያስ በበኩላቸው የ”ጊያ ካንሶ” ክብረ በዓል የ”ጎፋ ጋዜ ማስቃላ” በዓል አካል ሲሆን የበዓሉን መጠናቀቅ የሚያመላክትና ፈጣሪ ለመጭው ዓመት በሰላም እንዲያደርስ ምኞታቸውን የሚገልጹበት አንድነታቸውንና አብሮነታቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉበት የደስታ በዓል መሆኑን ተናግረዋል።

በዓሉ ከጥንት ጀምሮ በወረዳው ሕዝብ ዘንድ በዓመት አንድ ጊዜ በወርሃ መስከረም የመስቀል በዓል ከተከበረ ከአንድ ሳምንት በኋላ በዕለተ ሐሙስ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ሲከበር መቆየቱን አስረድተዋል።

የ”ጊያ ካንሶ” ባህላዊ ክብረ በዓልን ጨምሮ ሌሎችን ተፈጥሯዊና ባህላዊ ቅርሶች እንዲጠኑ፣ እንዲታወቁና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲያበረክቱ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የጎፋ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ድንበሩ ድርቤ በበኩላቸው በዞኑ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች መኖራቸውን ገልጸው እነዚህን ሀብቶች ጥናትና ምርምር በማድረግ ይበልጥ እንዲለሙና እንዲታወቁ ይሰራል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ ከሚያለያዩን ይልቅ አንድነታችንን የሚያጠናክሩ ባህላዊ እሴቶች በርካታ መሆናቸውን አንስተው አብሮነትና ወንድማማችነትን በማጎልበት ጠንክረን በመስራት ዞኑን የብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የጎፋ ጋዜ ማስቃላ ማጠቃለያ የሆነው ይህ ድንቅ ባህላዊ እሴት በዩኒስኮ እንዲመዘገብ ዞኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች በበኩላቸው አባቶቻችን ለዘመናት ጠብቀው ያቆዩትን በዓል ሳይበረዝና ሳይከለስ ለመጭው ትውልድ እንዲተላለፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በበዓሉ ላይ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ የአካባቢው የባህል መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን