ሀዋሳ፡ መስከረም 22/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ በሚሰጠው ፈተና የተማሪዎች ውጤት የተሻለ እንዲሆን ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ አሳሰበ፡፡
ቢሮው “የላቀ ትጋት ለትምህርት ጥራትና ለሀገር ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ የትምህርት ሳምንት አከባበር ጉባኤ አካሂዷል።
የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘማች ክፍሌ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ የትምህርት ዘርፍ በርካታ ባለድርሻ ተዋናዮች የሚሳተፉበት በመሆኑ በጉባኤው ከተማሪው እስከ ክልሉ ያሉ ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸው ለየት ያደርገዋል፡፡
የጌዴኦ ዞን አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ በበኩላቸው የትምህርት ፖሊሲ ወጥ ባለመሆኑና የትምህርት ሥርዓቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግር ውስጥ እየገባ መምጣቱ ቆም ብለን እንድንነጋገር ማሳያዎች በመሆናቸው ተሰባስቦ መወያየት አስፈላጊ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ያጋጠመውን የትምህርት ስብራት ለመጠገን ሁሉም ባለድርሻዎች እኩል ኃላፊትነት እንዳለባቸው ተገንዝበው ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡
ተማሪው፣ መምህርና የተማሪ ወላጆች በትምህርት ሥራ ዋነኛ ምሰሶዎች እንደመሆናቸው ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ አስተዳዳሪው ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) በዚሁ ወቀት እንደተናገሩት፤ ለዜጎች ጥራት ያለውን ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡
በትምህርት ሥራ ላይ በሚስተዋሉ ህጸጾችን ደጋግሞ በመነጋገር ፍትሀዊ የሆነ የትምህርት ተደራሽነት በማስፈን የሀገራችንን ብልጽግና እውን ለማድረግ መረባረብ እንደሚያስፈልግም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ በሚሰጠው ፈተና የተማሪዎች ውጤት የተሻለ እንዲሆን ለማድረግ በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት የቢሮው ኃላፊው ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ቢሮው በትምህርት ዘመኑ ከ1.9 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ተቀብሎ ለማስተማር አቅዶ ወደ ትምህርት ገበታ የመጡ ተማሪዎች 73 በመቶ ብቻ መሆናቸውን የገለጹት ዶክተር አበባየሁ ወላጆች ሳይመዘገቡ በቤታቸው ያሉ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡ እምነት ሽፈራው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የሚባክነውን የህዝብና የመንግሥት ሀብት ማዳን መቻሉ ተገለጸ
ቅንጅታዊ አሠራርን በማስፈን ጥምር ደን መጠበቅ፣ ማስፋትና መጠቀም እንደሚገባ ተጠቆመ
የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በማዘመን የዘርፉን ውጤታማነት ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ