ሀዋሳ፡ መስከረም 22/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሙስናና ብልሹ አሰራር ሊመዘበር የነበረ ከ95 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።
የፀረ ሙስና ትግሉን ለማጠናከር የሚያስችል ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና ስልጠና መሰጠቱም ተጠቁሟል።
የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን መጪው ትውልድ በስነ ምግባር የታነፀ ዜጋን በመፍጠር ሙስናና ብልሹ አሰራርን ትውልዱ እንዲጠየፍ እንደሀገር እየሰራ የሚገኝ ተቋም ለመሆኑ ተመላክቷል።
ባለፉት ዓመታት ከ550 በላይ በሚሆኑ የጥቆማ አማራጮች ወደ ተቋሙ የቀረቡለትን መነሻ በማደረግ በተከናወኑ ተግባራት ከ95 ሚሊዮን ብር በላይ ይመዘበር የነበረውን የህዝብና የመንግስት ሀብትን መከላከልና ማዳን መቻሉን ምክትል ኮሚሽነርና የሙስናና ብልሹ አሰራር መከላከል ዘረፍ ኃላፊ አቶ ዳግም ዳንኤል ተናግረዋል።
እንዲሁም በዓይነት ከተፈጸመ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ በከተማ 2ሺህ 237 ሄክታር እና በገጠር 1ሺህ 927 ሄክታር መሬቶችን ማስመለስ መቻሉን ኃላፊው አብራርተዋል።
ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በሚደረገው ርብርብ ከክልል ጀምሮ እስከ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የመንግስት አመራር የሀብት ምዝገባ እንዲያካሄድ በተደረገው ጥረት ከ8ሺህ በላይ የሚሆኑት ማስመዘገባቸውን አቶ ዳግም አሰረድተዋል።
ሙስናና ብልሹ አሰራር በሀገረም ሆነ በግለሰብ ላይ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈጥር በመሆኑ በዘረፉ የሚደረገውን ትግል ማጠናከር ወሳኝ በመሆኑ ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና ስልጠና መሰጠቱን ምክትል ኮሚሽነርና ትምህርትና ስልጠና አውታሮች ዘረፍ ኃላፊ አቶ ታደሰ አይበራ ገልፀዋል።
በየጊዜው በተሰጡ ትምህርትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን የማጋለጡ ሂደት ህብረተሰቡ አጠናክሮ ከመቀጠሉም ባለፈ በባለቤትነት ጉዳዩን እያዩ መምጣታቸው የሚበረታታ እንደሆነ ኃላፊው ተናገረዋል።
በዚህም በቢጣ ወረዳ 2 ሚሊዬን 85 ሺህ፣ ጋቺት ወርዳ 1ሚሊዬን 186 ሺህ፣ በሼይ ቤንች ወርዳ ከ 4 ሚሊዬን ብር በላይ ከህዝብ የተሰበሰበ የጤና መድን ገንዘብ ለታለመለት ዓለማ ያልዋለ መሆኑ በአገለግሎት አሰጣጥ ላይ ክፍተት የሚፈጥር እንደሆነና በቀጣይም ባለድርሻ አካላት በተገቢው ሊመሩ እንደሚገባም አቶ ታደሰ አስገንዘበዋል።
በተለይም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማቶችና በትምህርት ቤቶች ስልጠናውን አጠናክሮ በመስጠት የአመለካከት ችግሮችን መቀረፍ የሚቻል እንደሆነ የገለፁት አቶ ታደሰ በህዝባዊ ተቋማትም በተደረገ ክትትል እየታዬ መምጣቱ ህብረተሰቡ በጥንቃቄ ሊመለከተው ይገባል ብለዋል።
ከህዝቡ የሚመጡ ጥቆማዎችን ወደ ተግባር በመቀየር ረገድ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ የገለፁት ኮሚሽነሮቹ ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመከላከል ረገድ ከተቋማት በተጨማሪ ህብረተሰቡና ሚዲያው የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዘበዋል።
ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የሚባክነውን የህዝብና የመንግሥት ሀብት ማዳን መቻሉ ተገለጸ
ቅንጅታዊ አሠራርን በማስፈን ጥምር ደን መጠበቅ፣ ማስፋትና መጠቀም እንደሚገባ ተጠቆመ
የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በማዘመን የዘርፉን ውጤታማነት ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ