በጎፋ ዞን የሣውላ ከተማ አስተዳደር ህዝብ ምክር ቤት ለ2017 ዓ.ም ዕቅድ ማስፈጸሚያ ከ393 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት አጸደቀ

ሀዋሳ መስከረም 21/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጎፋ ዞን የሣውላ ከተማ አስተዳደር ህዝብ ምክር ቤት ለ2017 ዓ.ም ዕቅድ ማስፈጸሚያ ከ393 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት አጽድቋል።

ምክር ቤቱ በካሄደው መደበኛ ጉባኤ  የከተማውን አመታዊ የስራ ሪፖርትና ዕቅድ እንዲሁም ልዩ ልዩ ሹመቶችን በማጽደቅ መጠናቀቁም ተመላክቷል።

ምክር ቤቶች  የህዝብ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ የህግ የበላይነትን በማስከበር የዜጎች መብትና ነጻነት እንዲከበር እና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን በማስቻል የህዝብ ውክልናን ማረጋገጥ እንደሚገባቸው ይታወቃል።

የሣውላ ከተማ ህዝብ ምክር ቤት አራተኛ ዙር 12ኛ የሥራ ዘመን በአራተኛ መደበኛ ጉባኤው የ2016 በጀት ዓመት  የአፈፃፀም ሪፖርትና እና የ2017 ዕቅድ ዙሪያ  መክሮ  በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።

የምክር ቤቱ አባላት  በከተማው የሚሰተዋሉ የንፁህ  መጠጥ ውሃ የፍጆታ ታሪፍ ጭማሪ በኦዲት ግኝት ዙርያ የሚሰተዋሉ የአሰራር ክፍተቶችና የቀበሌ መቆቅሮችን ከመደገፍ አንጻር  የሚስተዋሉ ክፍተቶችን አንስተዋል።

ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ የልማትና የመልካም አሰተዳደር ጥያቄዎች የጽ/ቤት ኃላፊዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን የሳውላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኢርቦላ ኢርኮ  ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በጉባኤው የከተማ አስተዳደሩን የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሪፖርትና ዕቅድም ቀርቦ ጸድቋል።

ለከተማ አስተዳደሩ የቀረበለትን የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ዕቅድ ለማስፈጸም 393 ሚሊዮን 327ሺ 497 ብር በጀት ተወያይቶ አጽድቋል።

የተመደበው የመንግስት በጀት ለታለመለት ዓላማ ብቻ በማዋል የከተማውን የውስጥ ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የምክር ቤቱ አባላት አሳስበዋል።

ምክር ቤቱ  የቀረበለትን ልዩ ልዩ የስራ ኃላፊዎችን ሹመት ተቀብሎ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።

ተሿሚዎች የተጣለባቸውን የመንግስትና የሕዝብ ኃላፊነትና አደራ በታማኝነትና በቅንነት እንዲወጡ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡ ስንታየሁ ሙላቱ – ከሳውላ ጣቢያችን