ሀዋሳ መስከረም 21/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በወላይታ ዞን የ2017 ዓ.ም ዞናዊ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር “የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ለብልፅግናችን!” በሚል መሪ ቃል በጉኑኖ ሐሙስ ከተማ ተጀምሯል።
የወላይታ ዞን ም/አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ዳንኤል ዳሌ በእንስሳት ሀብት አርሶአደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረውን ርብርብ ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ የቆዩ ችግሮችን በመፍታትና ከዚህ በፊት የነበሩ ተሞክሮችን ማስፋትና ማጎልበት እንደሚገባም ገልጸዋል።
በዘንድሮው በጀት ዓመት 13 ሺህ 990 ውስጥ 5623 ጥጆችን ለማግኘት ግብ ተጥሎ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
የእንስሳቱ ዘርፍ አርሶአደሩን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ገበያን ለማረጋጋትና ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥር በመሆኑ በየደረጃው የሚገኘው አመራር ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ስራውን በላቀ ቁርጠኝነት እንዲመራው በአጽንኦት አሳስበዋል።
እንደሀገር የተጀመረው የሌማት ትሩፋት የቤተሰብ ብልፅግና ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት የጠቀሱት ም/አስተዳዳሪው የወተት መንደር ለመፍጠር ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የተጀመረው የዘንድሮው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ከአምናው የተቀመሩ ተሞክሮዎችን በመተግበር በተሻለ ደረጃ ለመፈጸም ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አመላክተዋል።
የተዳቀሉ ጥጆች እስከሚወለዱ ድረስ የመከታተልና የመደገፍ ስራ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ዛሬ የተጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ በሁሉም አከባቢዎች ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።
የጉኑኖ ሐሙስ ከተማ ከንቲባ አቶ ብርሃኑ ዋጃ በበኩላቸው በእንስሳት ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም ተጠቅሞ ከግብናው ዘርፍ የሚመነጨውን ኢኮኖሚ በማሳደግ አርሶ አደሩን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን ማስፋፋት ወሳኝ ነው ብለዋል።
በከተማው የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት በቂ የሆርሞንና የማዳቀያ ቁሳቁስ እንዲሁም የባለሙያ ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል።
በመርሃግብሩ የወላይታ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዘውዱ ሳሙኤልን ጨምሮ ሌሎች የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ በቀለች ጌቾ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ