በየም ብሄረሰብ ዘንድ በልዩ ድምቀት የሚከበረው የሄቦ በዓል ያለፈውን ዓመት ወደ ማይመለስበት አሰናብቶ አዲስ ዓመትን በናፍቆትና በጉጉት የሚቀበሉበት ነው፡፡
በበዓሉ ላይ በእድሜ የገፉ ሽማግሌዎች ሴቶችና ወጣቶች እንዲሁም ህጻናት ሳይቀሩ በማክበሪያ ቦታዎች “ካንቻ” ላይ ባህላዊ ዜማዎችን እያዜሙ ይጫወታሉ፡፡
በዚህ ማክበሪያ ቦታ “ካንቻ” ከጥንት ጀምሮ ሁሉም የማህበረሰብ አባላትን ባሳተፈ መልኩ እየተከበረ የመጣ ነው፡፡ በማክበሪያ ቦታው ባህላዊ እሴቶችን የሚገልጹ የተለያዩ ባህላዊ የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያዎች ለስርዓቱ ማስፈጸሚያነት ይውላሉ፡፡
ለመስቀል በዓል ወቅት ብቻ ከሚዉለዉ የትንፋሽ ሙዚቃ መሳሪያዎች መካከል መለከት ወይም በብሔረሰቡ ቋንቋ “መርካታ”ና “ፊኖ” የተሰኙ የትንፋሽ ሙዚቃ መሳሪያዎች ተጠቃሽ ናቸዉ፡፡
“ፊኖ” ከቀርከሃ የሚዘጋጅ ነው፡፡ ከድኩላ ቀንድ የሚሰራዉ ደግሞ መለከት ወይም በብሔረሰቡ ቋንቋ “መርካታ” ይባላል:: በዝግጅቱ ላይም ልምድ ያላቸው የብሔረሰቡ ተወላጆች ይሳተፋበታል፡:
የትንፋሽ ሙዚቃ መሳሪያው ቅኝት እንደ ዘመናዊ መሳሪያ ሁሉ ዜማ እንዲፈጥር ተደርጎ የተቃኘ ነው፡: ለዚህም ነዉ በቡድን ሆነዉ በሚጫወቱበት ወቅት እጅግ ድንቅ ሞገስ ያለው ድምፅ የሚፈጥረዉ፡፡
“ፊኖ” የሄቦ በዓል እስኪጠናቀቅ ድረስ በካንቻ/የጭፈራው ቦታ/ ይቀመጣል፡፡ ጨዋታውን አቋርጦ ለመሄድ የሚፈልግ ሰው ቢኖር እንኳን ፊኖውን ዛፍ ስር አስቀምጦ ይሄዳል፡፡ ጨዋታው የተጠናቀቀ ዕለት የፊኖውን ደህንነት ጠብቆ በማስቀመጥ በዓመቱ እንደገና የሚያመጣ ሰው ይመረጣል።
ባህላዊ መሳሪያው የሄቦ በዓል ስነ ሰርዓት ከተጠናቀቀ ጊዜ ጀምሮ ሰብስቦ በማስቀመጥ በየዓመቱ ይጠቀሙታል::
ይህን አኩሪ የትንፋሽ ሙዚቃ መሳሪያ ከዘመናዊ ሙዚቃ መሳሪያ ጋር የሚስተካከል ቅኝት ያለው በመሆኑ መሳሪያውን ይበልጥ በማስተዋወቅ በዘመናዊ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ የራሱን አሻራ እንዲያበረክት ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይጠይቃል::
ዘጋቢ፡ ተዘራ በቀለ- ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
አጀንዳዎችን በማሰባሰብ የህዝቡ ጥያቄ በተገቢው እንዲመለስ የምክክሩ ሂደቱ የላቀ አስተዋፅኦ እንዳለው ተሳታፊዎች ገለፁ
እንደሀገር ካለንበት ችግሮች ወጥተን ዜጎች ተረጋግተው የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን ምክክሩ እንደሚያግዝ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊ አካል ጉዳተኞች ተናገሩ
የጂንካ ዩኒቨርስቲ ለኤሶል ልዩ አዳሪ ትምህርት የተለያዩ ድጋፎችን አደረገ