በየም ብሄረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጎ በልዩ ትኩረት ከሚከበሩ በዓላት መካከል የ“ሄቦ” በዓል ዋነኛው ነው፡፡ የሄቦ በዓል አከባበር መቼ እንደተጀመረ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም ከጥንት ጀምሮ እንደ ዘመን መለወጫነት የሚከበር የብሔረሰቡ ባህላዊ በዓል ነው፡፡ በዞኑ የሚገኙ ሁሉም የእምነት ተከታዮች ሄቦን እንደ ዘመን መለወጫ በዓል ያከብሩታል፡፡
ለበዓሉ አከባበር የሚደረጉ ዝግጅቶች
ቁጠባ
ለሄቦ በዓል አባዎራዎች፣ እማዎራዎችና ወጣቶችም ጭምር የረዥም ጊዜ (የዓመት) ቁጠባ ያደርጋሉ፡፡ የገንዘብ ቁጠባ የሚደረግባቸው ሁለት መንገዶች ሲኖሩ እነዚህም ዕድር በመግባትና ዕቁብ በመጣል ይሆናል፡፡ የገንዘብ ቁጠባውም ዋና ዓላማው ለበዓሉ ለሚሆን ለሥጋ ዕርድ ወጪ እና ለአልባሳት ግዥ ይሆናል፡፡ በብሄረሰቡ ዘንድ የሄቦን በዓል በደመቀ ሁኔታ ለማክበር የዓመት ዝግጅት ይደረጋል፡፡
የብቅል ዝግጅት
ለክብረ በዓሉ ከሚዘጋጁ ዋነኛው ባህላዊ የመጠጥ ዓይነቶች መካከል የማ ኡሻ ወይም /ቺፋ/ (ቦርዴ) ይባላል፡፡ ይህ የመጠጥ ዓይነት ከገብስና ቀይ ጤፍ የሚዘጋጅ ሲሆን ለዚህ መጠጥ ሴቶች ቅድመ ዝግጅት ከሚያደርጉት ተግባራት አንዱ የብቅል ዝግጅት ነው፡፡ ከጥር ወር ጀምሮ ያበቅላሉ፡፡
የኮባና ዝግጅት
የሄቦ በዓል ሲቃረብ የሴቶች የመጀመሪያ ሥራ የሚሆነው ለበዓሉ የሚሆን ‹‹ኮበና›› (የቆጮ ድፎ) እንሰት መፋቅ ነው፡፡ ከበዓሉ ቀደም ተብሎ እንሰት ተፍቆ ይዘጋጅና ለበዓሉ መከበር አራትና ሦስት ቀናት ሲቀሩት ቆጮው ተቆርጦ ኮበና ይጋገራል፡፡
የጎቶ ዝግጅት
በሄቦ በዓል በወንዶች ከሚደረጉ ዝግጅቶች አንዱ ‹‹ጎቶ›› (የማገዶ እንጨት) ነው፡፡ በየም ብሄረሰብ የሄቦ በዓል በሚከበርበት ወቅት ለእንጨት ሰበራ ወደ ጫካ አይኬድም፡፡ በበዓሉ ሰሞን እሳት ከቤት እንዲጠፋ አይደረግም፣ ስለዚህም እሳት ከቤት እንዲጠፋና ማንኛውም ለበዓሉ የሚሆን የምግብ ዝግጅት ሥራ የተቀላጠፈ እንዲሆን የማገዶ እንጨት ለበዓሉ 2 ወር ሲቀረው ይፈለጥና በጎጆ ቤት ቅርፅ ተከምሮ ደርቆ ለበዓሉ ምግብ ማብሰያ ያገለግላል፡፡ ይህ የማገዶ እንጨት ክምር ጎቶ ተብሎ ይጠራል፡፡
የዱዋ (የግንድ ጉማጅ) ዝግጅት
በሄቦ በዓል ወቅት እሳት ከቤት እንዳይጠፋ ስለሚፈለግ ክብረ በዓሉም እስኪጠናቀቅ የሚቆይ ዱዋ /ወፍራም የማገዶ ግንድ ጉማጅ ምድጃ ውስጥ ይቀመጣል፡፡ በግንዱ ላይ የተቀጣጠለው እሳት በዓሉ እስኪጠናቀቅ እንዲቆይ ይደረጋል፡፡ ቢያልቅም እንኳ በምትኩ ሌላ ይተካል፡፡
የሄቦ በዓል አከባበር ሂደት
መስከረም 14 ቀን
በዓሉ መከበር የሚጀምረው ከመስከረም 14 ቀን ጀምሮ ነው፡፡ መስከረም 14 ቀኑ ‹‹ካማ ኬሳ›› ይባላል፡፡ ይህ ቀን በቤተሰብ ውስጥም ሆኖ በዘመድ አዝማድ መካከል የተፈጠረ ቅራኔና የሰነበተ ቂም ካለ በሽማግሌዎች አማካይነት የእርቅ ሰላም ስርዓት የሚፈፀምበት ቀን ነው፡፡ ይህ ‹‹የካማ ኬሳ›› ሥርዓት የሚደረግበት ዋነኛ ምክንያት ቂም ይዞ ወደ አዲሱ ዓመት ማሻገር የተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶችን ሊፈጥር ይችላል ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ በመካከላቸው ቅራኔ ያለባቸው ግለሰቦች በሽማግሌዎች ፊት ቀርበው ይቅር ይባባላሉ፡፡ በመቀጠልም ይቅርታ መጠያየቃቸው ተምሳሌት የሚሆን ከሁለቱ ወገን መፅዋዕት ማር ይቀርባል፡፡ የቀረበላቸውን ማር በቅጠል ይዘው በጎሳ መሪያቸው ፊት ቀርበው እንዲቀምሱ ይደረጋል፡፡ በመጨረሻም ‹‹ሹማ›› ቦርዴን በአንድ ዋንጫ በጋራ እንዲጠጡ ይደረጋል፡፡ ይህ የሚደረግበት ምክንያት ከአሁን በኋላ ታርቀናል፤ በፍቅር እንኖራለን የሚል ተምሳሌት ስላለው ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ መፅዋዕት ማቅረብ እየቀረ መጥቷል፡፡
መስከረም 15 ቀን
መስከረም 15 ቀን ኢፍቱ ይባላል፡፡ በየም ብሄረሰብ ዘንድ ኢፍቱ የንፃት ቀን ተብሎ ይወሰዳል፡፡ በዚህም ቀን የግልና የአካባቢ ንፅህና ተደርጎ የሚጠናቀቅበት እና የሆድ ህመም እንዳይከሰትና የምግብ ፍላጎትን እንዳይዘጋ ጎመንና ኖዕሚያ የተባለ የተክል ዓይነት ቅጠሉ ተከፍሎ የተዘጋጀው ገንፎ ‹‹ዳኣ›› የሚበላበት ቀን ነው፡፡
መስከረም 16 ቀን
መስከረም 16 ቀን ኣመቱ ይባላል፡፡ ‹‹ኣመቱ›› የሄቦ በዓል ዋዜማ በመባል በየም ብሔረሰብ ዘንድ ይከበራል፡፡ ይህ ቀን የበዓሉን ጌታ ‹‹ሳማ ጎር›› አቀባበል የሚደረግበት ቀን ነው፡፡ በዚህ ዕለት በርካታ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡
ለምሳሌ፡- ጎቶ ከተከመረበት የሚጓጓዝበት፣ ለቤት ጉዝጓዝ፣ የሚታጨድበት ደመራ በዓይነት ሁለት ይደመራል፡፡ የመጀመሪያው በቤተሰብ ሆኖ በምሽት ይቃጠላል፡፡ ሌላኛው ከሌሊቱ 9 ሰዓት ጀምሮ በአካባቢው ነዋሪዎች በህብረት የሚለኮስ ነው፡፡
ደመራ ከመለኮሱ በፊት አባወራ በትንሹ በተዘጋጀው ደመራ ለኩሰው የጎመን ምንቸት ይውጣ፤ ጥጋብ ይግባ በማለት ከጓዳ ከመኝታና ከሌሎች ቦታዎች ሁሉ አዳርሰው እስከ ደጅ በራፍ ይሸኛሉ፡፡ በመቀጠልም ‹‹ካሻ›› የተባለውን የአምቾ አይነት ከእንሰት ተዘጋጅቶ የበሰሉትን የቤቱ አባወራ በቅጠል ይዘው ‹‹ሳማጎሮ›› በማለትም ዓመቱን የሰላም ያድርግልን በማለት ከቤታቸው እስከ ደጅ ድረስ ይበትናሉ፡፡ በቅርብ ባለው ማሳው ድረስ በመሄድም ይበትናሉ ዘንድሮ በሰላም በጤና አድርሰኸናል የዛሬ ዓመትም በሰላም አድርሰን፤ ለምስጋና ዕድሜ ይኑረን፡፡ እህሉም ፍሬያማ ይሁን፤ ጎታራው ይሙላ በማለት ከበተኑ በኋላ ቀሪውን በማሳው መሃል አስቀምጠው ይመለሳሉ፡፡ በተመሳሳይ መልክ እማወራዋም በተራዋ ከቤት እስከ እንሰት ማሳ ድረስ በመሄድ ጓዳዋ፤ ጓሮዋና እንሰቱ የተባረከ እንዲሆን ተማጽና ትመለሳለች፡፡ መስከረም 17 ቀን ኢሶንሲ ፊና /አንደኛ ፊኖ/ በዓል፡- መጀመሪያ ዕለት በብሄረሰቡ ዘንድ መስከረም 17 ኢሶንሲ ፊና ወይም የመጀመሪያው ቀን እየተባለ ይጠራል፡፡
ፉርዕኒ ኦቱ/መልካም ምኞት መግለጫ
በብሄረሰቡ ዘንድ በሄቦ በዓል ወዳጅ ዘመድ እርስ በርስ የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞት በመግለፅ ለበዓሉ የተዘጋጀውን ምግብ አብሮ ይቋደሳል፡፡ በየዓመቱም ወዳጅ ዘመዶች የሚጠያየቁበትና የሚገባበዙበት ቋሚ ቀን አላቸው፡፡
በዚህ ቀን ልጆች ለበዓሉ ቀድሞ ከተዘጋጀው አንድ ትልቅ ፍልጥ እንጨት በመያዝ ወደ ወዳጅ ዘመዶቻቸው በመሄድ ይዘው የሄዱትን የጉቶ ፍልጥ ይዘው ወደ ቤት ሲገቡ ‹‹ቺፋሶ ማኣሪክ ኬፕሰፋኒያ›› (መጠጡን በሰላም ጠጣችሁ ወይ) በማለትና መልካም ምኞታቸውን በመግለፅ የወሰዱትን ፍልጥ ወደ ምድጃውና ምሰሶ አጠገብ ያስቀምጣሉ፡፡ በዚህም ጊዜ የቤቱ አባወራና እማወራ ኡሽኒ ጎር ዎታውቶ (ጠጥተናል ጎር ይባርካችሁ) በማለት ይመርቃሉ፡፡ ለበዓሉ የተዘጋጀው ምግብና መጠጥ ቀርቦ ከተመገቡ በኋላ በተመሳሳይ ጎር ዎታውቶ (የሄቦ ጌታ) ይባርካችሁ) በማለት ወደየቤታቸው ይመለሣሉ፡፡
ይህ በሄቦ በዓል ከወዳጅ አዝማድ ጋር የሚደረገው መገባበዝና የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞት ልውውጥ ፉርኒ ኦቱ (የአበባ መለዋወጥ) ይባላል፡፡
የቦጋ ጨዋታ፡- ‹‹ቦጋ›› ማለት ማፍረስ /መበዝበዝ ማለት ሲሆን ተጨዋቾቹ ቦጊኛ ይባላሉ፡፡ ይህ ጨዋታ የመጀመሪያው የሄቦ በዓል ከገባ ጊዜ ጀምሮ ባለው የቀን አቆጣጠር ‹‹ኡሺ ፊና›› /አምስተኛ ፊኖ ወይም መስከረም 21 ይጀመራል፡፡
የቦጋ ጨዋታ የሚካሄደው በየጎጡ ተከፋፍሎ ሲሆን ቦጊኛዎቹ ለጨዋታው ማድመቂያ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ይጠቀማሉ፡፡ እነዚህም ጌባ/ጋሻ፣ የጉረዛ ቆዳ፣ የድኩላ ቀንድ፣ ወዘተ በመጠቀም የቦጋ ጨዋታን በልዩ ሁኔታ ያደምቁታል፡፡
የቦጋ ጨዋታ የራሱ የሆነ ሥርዓት አለው፡፡ ማንም በዘፈቀደ አይንቀሳቀስም፡፡ በመሆኑም ጨዋታውን የሚመታ መሪ ይመረጣል፡፡ ይህ መሪ አባ ሚላ ይባላል፡፡ አባ ሚላ በጨዋታው መካከል ግጭት እንዳይፈጠር፣ ልጆች ጨዋታውን እንዳያበላሹ ጨዋታው በሰዓቱ እንዲጀመር እና በስንት ሰዓት ተጀምሮ በስንት ሰዓት ማለቅ እንዳለበት በቦግኛዎቹ ግንዛቤ ይሰጣል ይመራልም፡፡
በየም ብሔረሰብ የጊዜ አለካክ ስሌት የራሱ የሆነ የዘመን አቆጣጠር አለው፡፡ በብሔረሰቡ ዘንድ ጳጉሜን ጨምሮ 13 ወራት ሲኖሩት እነዚህም እንደሚከተለው ተመላክተዋል፡፡
የፊና (ፊኖ) ጨዋታ፡- እንደየአካባቢው ሁኔታ አጀማመሩ ይለያያል፡፡ በመጀመሪያው ቀን በኢሶኒሲ ፊኖ ካልተጀመረ በ4ኛው ቀን ይጀምራል፡፡ የመጀመሩ ሥርዓት ‹ኮምሱ› ይባላል፡፡ እንደ ልምምድም ነው፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ የካኛዎች ግጥሚያ ሥርዓት ይካሄዳል ይህም ኬጱ ይባላል፡፡ ከኬጱ ሥርዓት በኋላ አባቶች ይመርቃሉ የበዓሉ ፍፃሜ ይሆናል፡፡
በአጠቃላይ በየም ብሄረሰብ ዘንድ የዘመን መለወጫ በዓል ትልቅ ግምት ተሰጥቶ የዓመት ዝግጅት የሚደረግበት፣ የቤት ውስጥ ቁሳቁስ በአዲስ የሚተካበት አዲሱን ዓመት ለመቀበል ቅራኒ ተወግዶ አዲስ አስተሳሰብ የሚያዝበት በአዲስ መንፈስ በደስታ ወደ ሥራ የሚገባበት ትልቁ የብሔረሰብ ክብረ በዓል ነው፡፡
ሄቦ በዓል ለማህበራዊ ትስስር ያለው ፋይዳ
የበዓሉ አከባበር (አገልግሎት)
ክብረ በዓል፡- ክብረ በዓሉን ይሁነኝ ብሎ ለያዘው ለየም ማኅበረሰብ የሚሰጠው ተግባር ይኖራል፡፡ ክብረ በዓሉ ለማህበረሰቡ ሦስት ተግባራት ወይም አገልግሎት ይሰጣል፡፡
1) ባህላዊ አገልግሎት(Cultural Function)፡- ክብረ በዓሉን አክባሪ የሆነው የየም ማኅበረሰብ ባህላዊ ማንነቱንና ባህላዊ እሴቶቹን ይገልጻል፤ ይበይናል፤ ዘላቂ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ ዘላቂ እንዲሆኑ ያደርጋል ሲባል ዋጋ ኑሯቸው እንዲቀጥሉ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ የክብረ በዓሉ በተደጋጋሚ መምጣት ያንን ክብረ በዓል የሚያከብረው ማኅበረሰብ ባህላዊ እሴቶች ምንድን ናቸው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሰጣል፡፡
2)ማኅበረሰባዊ አገልግሎት (Sociological Function)፡- በክብረ በዓሉ አክባሪዎች (ተሳታፊዎች) መካከል የጠበቀ ትሥሥርና ወዳጅነት እንዲኖር ያደርጋል፡፡ በክብረ በዓሉ ጊዜ ግጭቶች (ለይቶላቸው) ወደ እርቅ እንዲመጡ ይደረጋል፡፡ (የተጣሉ ሰዎች በክብረ በዓሉ ጊዜ ይታረቃሉ ማለት ነው፡፡)
3)ሥነ ልቦናዊ አገልግሎት (Psychological Function)፡- በክብረ በዓሉ አክባሪዎች (ተሳታፊዎች) ዘንድ የደስታ፣ የእርካታና የነፃነት ስሜት ይፈጥራል፡፡
በአጠቃላይ በየም ብሄረሰብ ዘንድ የዘመን መለወጫ በዓል ትልቅ ግምት ተሰጥቶት የዓመት ዝግጅት የሚደረግበት፣ የቤት ውስጥ ቁሳቁስ በአዲስ የሚተካበት አዲሱን ዓመት ለመቀበል ቅራኔ ተወግዶ አዲስ አስተሳሰብ የሚያዝበት በአዲስ መንፈስ በደስታ ወደ ሥራ የሚገባበት ትልቁ የብሔረሰቡ ክብረ በዓል ነው፡፡
ምንጭ፡ የየም ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ