በወረዳ የ2016 ዓ.ም የወጣቶች የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የማጠቃለያ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡
በ2016 የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት በ16 የትኩረት መስኮች የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን 3 ሚሊየን 256 ሺ ብር የመንግስትን ወጪ ለማዳን ታቅዶ 8 ሚሊየን 556 ሺ ብር የመንግስትን ወጪ ማዳን መቻሉን የበና ፀማይ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደለልከኝ ሰኒ ተናግረዋል ፡፡
በዚህ የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት ድጋፍና እገዛ ለሚሹ አረጋዊያንና አቅመ ደካሞች 37 አዲስ ባህላዊ የሳር ቤት ግንባታ 38 የእድሳት እንዲሁም 8 አዲስ የቆርቆሮ ቤት ግንባታ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዉ በማጠቃለያ መርኸ ግብሩ ዕለት ከተሰሩ አዳዲስ የቆርቆሮ ቤቶች አራቱ ተጠናቀው ርክክብ የተፈፀመ ሲሆን ቀሪ ቤቶች በቅርብ ቀን ተጠናቀዉ ለአቅመ ደካማ እናቶች እንደሚያስረክቡም ኃላፊዉ አብራርተዋል፡፡
የበና ፀማይ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮሐንስ ጋርሾ በ2016 የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት በተሰሩ የተለያዩ ተግባራት ካለፉት አመታት የተሻለ ዉጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
በተለይ ቤት አጥተዉ በየሰዉ ቤት በጥገኝነት የሚኖሩና ዝናብ በመጣ ቁጥር ሲጨነቁ ለነበሩ አቅመ ደካሞች አካል ጉዳተኞችና አረጋዊያንን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንና በቀጣይ ጊዜያት ወጣቶችን ባለሀብቶችንና በጎ አድራጊ አካላትን በማስተባበር ሌሎች ይህን እድል ያላገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ኦሞ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተመስገን ጋርሾ በበኩላቸዉ ወጣቶች በእረፍት ጊዜያቸዉ የማህበረሰቡን ችግር በሚቀርፉ ተግባራት መሳተፋቸዉ ለራሳቸዉም የህሊና እርካታ ከማስገኘት ባሻገር መንግስት ገንዘብ አውጥቶ ለሚፈፅማቸዉ ተግባር አጋዥ እንደሚሆኑ ተናግረው በበናፀማይ ወረዳ በክረምት ወራት በወጣቶች በጎ ተግባር የተሰሩ ስራዎች የሚበረታቱ በመሆናቸዉ ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል ፡፡
የሉቃና የጉርዶ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት በረከት ቡሎ እና አርብቶ አደር ባንቲ በላቸዉ በሰጡት አስተያየት በቀበሌያቸዉ በተሳተፉባቸዉ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ በማድረጋቸዉ ደስተኞች እንደሆኑ ተናግረዋል ፡፡
የመኖርያ ቤት የተበረከተላቸዉ የቀይ አፈር ከተማ ነዋሪ ወ/ሮ አልማዝ አርከማል እና ወ/ሮ ሰረ ደለ በተደረገላቸዉ ድጋፍ መደሰታቸዉን ተናግረው ምስጋናቸዉንም አቅርበዋል፡፡
በዕለቱ የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ቀበሌያት ሴክተር መስርያ ቤቶችና ግለሰቦች የዋንጫና የስርተፍኬት ሽልማቶች ተበርክተዋል ፡፡
ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ- ከጂንካጣቢያችን
More Stories
አጀንዳዎችን በማሰባሰብ የህዝቡ ጥያቄ በተገቢው እንዲመለስ የምክክሩ ሂደቱ የላቀ አስተዋፅኦ እንዳለው ተሳታፊዎች ገለፁ
እንደሀገር ካለንበት ችግሮች ወጥተን ዜጎች ተረጋግተው የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን ምክክሩ እንደሚያግዝ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊ አካል ጉዳተኞች ተናገሩ
የጂንካ ዩኒቨርስቲ ለኤሶል ልዩ አዳሪ ትምህርት የተለያዩ ድጋፎችን አደረገ