በወላይታ ዞን በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው “ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” አካል የሆነው በውሃና ድምፅ ብክለት ላይ ግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ ተካሂዷል።
ከአካባቢ ብክለት የተነሳ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችል የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጴጥሮስ ወ/ማርያም ጠቁመዋል፡፡
በከተማው የሚፈቀዱ ፕሮጀክቶች በዋናነት የፋብሪካ ተረፈ ምርቶች እና የቆሻሻ አወጋገድ ትኩረት ካልተሰጣቸው ችግሩ ሊባባስ እንደሚችል ጠቁመዋል።
በተለይ ከድምፅ ብክለት አኳያ ከተሽከርካሪዎች፣ ከእምነት ተቋማት፣ ከፋብሪካዎች የሚወጡ ከፍተኛ ድምጾች ለኅብረተሰቡ ዕረፍት የሚነሱ በመሆኑ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አጽንኦት ተሰጥቷል።
ዘላቂ መፍትሄ ካልተበጀ በከተሞች አካባቢ የሚስተዋሉ የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ለኅብረተሰቡ ጤና ጠንቅ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ በተፈጥሮና በሰው ልጆች የመኖር ህልውና ላይ እያስከተለ ያለው ዘርፈ ብዙ ችግሮችንና ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የሁሉንም ሰው ርብርብ ይሻል ብለዋል።
የአካባቢ ብክለትን የሚያስከትሉት የፕላስቲክ ብክለት፣ የአየር ብክለት፣ የውሃ ብክለት፣ የአፈር ብክለት፣ የድምጽ ብክለትና የአደገኛ ቆሻሻ ወይም የኬሚካል ብክለት መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ለአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮች የሰዉ ልጆች የመኖር መብታቸዉን በመጋፋት ለምግብ ዋስትና እጥረት በተለይ ለተላላፊ በሽታዎች፣ ለስደት፣ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀዉሶች እያጋለጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አካባቢን መጠበቅ በተለይም የሰዉ ልጆች ደህንነትን መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት በመሆኑ ትኩረት ሰጥተን መሥራት ይገባናል ብለዋል፡፡
የአካባቢ ብክለት በአየር ንብረት ለዉጥ ላይ የሚያስከትለዉን ተጽዕኖ ለህብረተሰቡ በተገቢው ግንዛቤ የማስጨበጫ ስራ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የወላይታ ዞን ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መርክነህ ማለዳ በበኩላቸው የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለዉጥ እያስከተለ ያለዉን ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችንና ቀዉሶችን ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች ተገንዝበው በመከላከሉ ላይ ርብርብ ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል።
አካባቢን ከውሃና ከድምፅ ብክለት ነጻ በማድረግ ንጹህና ለኑሮ ተስማሚ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በሶዶ ከተማ ያለው የቆሻሻ ውሃ አወጋገድ በተለይ በማረሚያና በቄራ አካባቢ የሚፈጠረው የአየር ብክለት በሕብረተሰቡ ጤና ላይ ችግር እየሆነ መምጣቱን አስተያየት ሰጪዎች ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፡ በቀለች ጌቾ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ