ሀዋሳ፡ መስከረም 15/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በወረዳው በትምህርት ዘርፍ እየገጠመ ያለውን የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል ለማስቀረት ሁላችንም የሚጠበቅብንን እንወጣለን ሲሉ በቡሌ ወረዳ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ፡፡
እየተመዘገበ ያለው ውጤት እንዳሳዘናቸውም ወላጆቹ ተናግረዋል፡፡
በወረዳው በሁለት ትምህርት ቤቶች የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች አንድ ተማሪ ብቻ ማለፊያ ውጤት አምጥቷል ተብሏል፡፡
ከተማሪ ወላጆች መካከል አቶ ኃይሉ ህርባና ሳሙኤል ኩርሴ በ6ኛ፣ በ8ኛና በ12ኛ ክፍል ተማሪዎች እየተመዘገበ በመጣው ውጤት ማዘናቸውን ጠቅሰው፥ ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው የመጣ ችግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሁሉም የሚጠበቅበትን በአግባቡ መወጣት አለበት ያሉት ወላጆች፥ ተማሪዎች ምን እየተማሩ እንደሆነ፣ የተሰጣቸውን የቤት ሥራ በተገቢው ሁኔታ መስራታቸውንና አለመስራታቸውን እንዲሁም ትምህርታቸውን በተገቢው እየተከታተሉ መሆናቸውን በመቆጣጠር የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ አንስተዋል፡፡
እርስ በርስ ከመወቃቀስ የትምህርት ዘርፍ ባለድርሻዎች፣ ተማሪዎችና ወላጆች በቅንጅት መስራት፣ አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የቡሌ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሰ መምህር ማረኝ ወራሳና የሱኮ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር በወረዳው የተስተዋለውን የውጤት መውረድን ለመቀልበስ ውጤት ሊያስገኝ የሚችል የጋራ ግብ አውጥቶ ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
የቡሌ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ከድር ያሲን ከትምህርት ሥርዓት ፖሊሲ መሻሻል ጋር ተያይዞ እየገጠመ ያለውን ቀውስ ለማስተካከል ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የትምህርት ቤቱን መሠረተ ልማት በማሻሻል፣ የትምህርት ግብዓት አቅርቦት በማመቻቸትና በችግሮች ዙሪያ ከባለድርሻዎች ጋር በመመካከር በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በወረዳው ከሁለት መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ከወሰዱት መካከል አንድ ተማሪ ብቻ ከ50 በመቶ ውጤት ማስመዘገቡ ተጠቁሟል፡፡
ዘጋቢ፡ እምነት ሽፈራው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ