በ2017 በጀት አመት 93 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱን የሣላማጎ ወረዳ ገቢዎች ልማት ፅህፈት ቤት አስታወቀ

ሀዋሳ፡ መስከረም 15/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኦሞ ዞን የሣላማጎ ወረዳ በ2017 በጀት አመት 93 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱን የወረዳው ገቢዎች ልማት ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የወረዳው ግብር ከፋዮች ግብርን በወቅቱ በመክፈል ለሀገራዊ ዕድገት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

በወረዳው ያነጋገርናቸው ግብር ከፋዮች እንደገለፁት የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ እንደሚከፍሉ ገልፀው የሀገርን ዕድገትና ልማት ለማፋጠን ሌሎችም ግብርን በወቅቱ እንዲከፍሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በደቡብ ኦሞ ዞን የሣላማጎ ወረዳ ገቢዎች ልማት ፅህፈት ቤት ምጣኔ ጥናት የታክስ ትምህርትና ቅሬታ አጣሪ ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ አቶ ኢሳያስ ላላ እንደገለፁት በተፈጠሩ የግንዛቤ ሥራዎች የተሻለ የገቢ አፈፃፀም መኖሩን ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በሁሉም የገቢ አርዕስቶች 93 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የገለፁት የሣላማጎ ወረዳ ገቢዎች ልማት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አማኑኤል ወይዶ ግብር ከፋዮች ለአከባቢያቸው ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል ፡፡

የወረዳው የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ሕጉ ቅጣቱ እንደገለፁት ሕብረተሰቡ የሚጠበቅበትን ግብር ከፍሎ አገልግሎት እንዲያገኝና የገቢ አቅምን አሟጦ ለመሰብሰብ አቅጣጫ ተቀምጦ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

ዘጋቢ: ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን