የመስቀል በዓል ገበያ የበሬ ዋጋ ከአዲሱ ዓመት የበዓል ገበያ ጋር ሲነፃፀር ጭማሪ እንዳለው በሀዋሳ ከተማ 01 ቀበሌ በሚገኘው የቁም ከብት ገበያ ገዢዎችና ነጋዴዎች ተናገሩ::
አቶ ጌታሁን ሻንካ፣ ወ/ሮ አበባ ካሳዬ እና አቶ ስዩም ጥላሁን የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ሲሆኑ በማህበር ለመስቀል በዓል ያጠራቀሙትን ገንዘብ ሀዋሳ 01 ቀበሌ በሚገኘው የቁም ከብት ገበያ ለመግዛት በመጡበት አጋጣሚ ነው ያገኘናቸው::
የመስቀል የእርድ በሬ ገበያ ከአምናው የዋጋ ጭማሪ እንዳለው ጠቁመው ከፍተኛው 120 ሺህ፣ መካከለኛው 75 ሺህ እንዲሁም ዝቅተኛው 65 ሺህ እንደሚገዛ ነው የገለፁት::
አቶ ጌታሁን ሻንካ እንደተናገሩት ዓመቱን ሙሉ ለመስቀል በዓል የቆጠቡትን ገንዘብ በማውጣት ጥሩ የሚባል ለቁርጥና ለክትፎ የሚሆን በሬ በ75 ሺህ ብር ገዝተዋል::
ወ/ሮ እልፍነሽ ሴዴቦ በበኩላቸው የእርድ በሬ በብዛት የገባ ቢሆንም ከአዲስ አመት ጋር ሲነፃፀር የ10 ሺህ ብር ጭማሬ እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል::
የበግና የፍየል ዋጋ ሲተይ ደግሞ ከፍተኛው 20 ሺህ፣ መካከለኛው 10 ሺህ እንዲሁም ዝቅተኛው 4ሺ 500 እንደሆነ የተናገሩት አቶ ትዕግስቱ አበራ ናቸው::
አቶ ወንድሙ ወጋሶ የእርድ በሬ ነጋዴ ሲሆኑ በዛሬው ገበያ የዋጋ ልዩነት እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
ሸማቾቹ ሲናገሩ የመስቀል በአል ተከፋፍለን በፍቅርና በደስታ የምናከብረው በዓል እንደመሆኑ መጠን አቅመ ደካሞችን በማሰብ ያለንን ማካፈል ይጠበቅብናል ብለዋል::
ሸማቾቹ ሀገራችንን ፈጣሪ ሰላም እንዲያደርጋት በመመኘት ለክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለመስቀል በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል::
ዘጋቢ: ሐና በቀለ
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ