በዘርፉ የሚታየውን ውስንነትና ህገ-ወጥነት ለማስቀረት የሁሉንም ርብርብና ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ተመላክቷል።
ይህ የተገለጸው ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር በአርባምንጭ ከተማ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ነው።
በመድረኩ ከደረጃ በላይ መድሀኒት መያዝ፣ በግል መድሀኒት መደብሮችና ማከፋፈያዎች የመንግስት የፕሮግራም መድሀኒቶችን ይዞ መገኘት፣ ያለ ሀኪም ትዕዛዝ መድሀኒት መሸጥ፣ የፍሪጅ ቴርሞ ሜትር አለመኖርና መሰል ችግሮች በስፋት የሚስተዋሉ እንደሆነ በውይይት ሰነዱ ቀርቧል።
በክልሉ ቅኝት በተደረገባቸው 143 በሚደርሱ የመድሀኒት መደብሮች፣ ማከፋፈያዎችና ድንገተኛ ቁጥጥር በተደረገባቸው ተቋማት በአመቱ ከ82 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ህገ-ወጥ መድሀኒቶችና የምግብ ምርቶች መወገዳቸውም ተብራርቷል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች እንደገለፁት እንደ ሀገር በመድሀኒት ረገድ የሚታየው ህገ-ወጥነት ህብረተሰቡን እየጎዳ በመሆኑ በዚህ ችግር ውስጥ ያሉ ሊታረሙና የቁጥጥር ስራው ሊጠናከር ይገባል።
በመንግስት ተቋም የሚገኙ የፕሮግራም መድሀኒቶች ተሰርቀው የሚወጡት ከመንግስት የጤና ተቋም በመሆኑ በዚህ ረገድ የቁጥጥር ስራው ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ሀዋሳ ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ንማኔ በምግብና በመድሀኒት ረገድ ህገ-ወጥነቱ እየሰፋ በመሆኑ ለመከላከል በጋራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶችና ግብአቶች ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ሶንቆ፤ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በስታንዳርዱ መሰረት አለመስራትና አለመከታተል፣ የግል ኪሊኒኮች የመድሀኒት መደብር እየሆኑ መምጣታቸውና ከደረጃ በላይ መድሀኒቶችን ይዞ መገኘት በስፋት እየተስተዋለ እንደሆነ አንስተዋል።
በአብዛኛው የግል የመድሀኒት መደብሮች ህገ-ወጥነት መስፋፋት፣ በምግብ እጥረት ለተጎዱ ህጻናት የሚመጣ ፕላምፕሌት በሸቀጣሸቀጥ ሱቆች እየተሸጠ መገኘቱ፣ የቁጥጥርና የክትትል ስራው ልልነትን የሚያሳይ በመሆኑ በቀጣይ ሁሉም ተቆርቋሪ በመሆን ህገ-ወጥነቱን በጋራ ማረም ያስፈልጋል ብለዋል።
ባዛሮች ላይ የሚቀርቡ ጥራታቸው ያልተረጋገጡ ምርቶችን መከታተልና ማስወገድ እንደሚገባና ደህንነታቸው ባልተጠበቀ መልኩ በህገ-ወጥ የሚዘዋወሩ መድሀኒቶችን በተገቢው መቆጣጠር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ሳጌ ሻምባ በዘርፉ የሚታየው ችግር ከግል ባሻገር በመንግስት የጤና ተቋማትም ጭምር በስፋት የሚታይ በመሆኑ ሁሉም ለማህበረሰቡና ለህሊናው ሲል ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በቀጣይ የህግ ማስከበር ስራውን በማጠናከር ህገ-ወጦች ላይ ርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል አቶ መንግሥቱ ደምሴና ነጋሽ አህመድ፤ ሀገር ውስጥ እንዳይሸጡ የተከለከሉ እና የፕሮግራም መድሀኒቶች በግል ተቋማት መገኘትና መሠል ችግሮች በህብረተሰቡ ላይ ሁለንተናዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ቅርንጫፍ
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ