የዩኒቨርስቲውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በቅንጅት ሊሠራ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 13/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዩኒቨርስቲውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከአካባቢው ማህበረሰብ እና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝ የጂንካ ዩኒቨርስቲ አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው ከሀይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክም አካሂዷል።

የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ብሎም የቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራትን  ማከናወን የሚቻለው የአካባቢውን ሠላምና ደህንነት በተገቢው ማስጠበቅ ሲቻል እንደሆነ የገለፁት የጂንካ ዩኒቨርስቲ የፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አምባ ጩፋ ናቸው ።

ሀላፊው አያይዘውም ሠላምና ፀጥታን በማስፈን ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር የሚቻለው ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሲያበረክት ነው ብለዋል።

በዩኒቨርስቲው የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕረዚዳንትና የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶክተር አለሙ አይላቴ እንደገለፁት ዩኒቨርስቲው ከአካባቢው ማህበረሰብና ከባለድርሻ አካላት ጋር በፈጠረው ቅንጅታዊ አሠራር ሰላማዊ የመማርና ማስተማር ከባቢ መፍጠር መቻሉን አመላክተዋል።

የጂንካ ዩኒቨርስቲ አዲስ በመሆኑ ከግንባታ ሥራዎች ጋር ተያይዞ የሚፈፀሙ አንዳንድ የስርቆትና አላስፈላጊ ተግባራትን ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት በትብብር እየተሰራ ነዉ ብለዋል።

ዩኒቨርስቲው ሠላምና ደህንነትን በማስጠበቅ የሚጠበቅበትን ሀላፊነት በተገቢው ለመወጣት ከአካባቢው ህብረተሰብና ከባለድርሻ አካላት ጋር የነበሩትን ቅንጅታዊ አሰራሮች አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ዶክተር አለሙ አስረድተዋል ።

የኣሪ ዞን ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ሀላፊ አቶ ማታዶ በርቢ እንደተናገሩት ዩኒቨርስቲው ለሚያከናውኗቸው ተግባራት ስኬታማነት የአካባቢውን ሠላምና ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ ዘርፈብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።

በዩኒቨርስቲው የፀጥታና ደህንነት ፅህፈት ቤት ሀላፊ ኮማንደር ካሳ ካዉዛ በበኩላቸው ከሕብረተሰቡ ጋር በሚያከናዉቸዉ ቅንጅታዊ አሰራሮች ዩኒቨርስቲው ያለምንም የፀጥታና ደህንነት ስጋት ሀላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

ዘጋቢ፡ ዳኜ ጥላሁን – ከጂንካ ጣቢያችን