በሸኮ ወረዳ የህብርተሰብ ተሳትፎ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ መስከረም 13/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሸኮ ወርዳ በ350 ሚሊዬን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለሚገነቡ የልማት ስራዎችና ፕሮጀክቶች የህብርተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ።

ፕሮጀክቱ በ 2ኛ ዓመቱ ከ 112 ሚሊዬን ብር በላይ ገቢ በህብረተሰብ ተሳትፎ ለማሰባሰብ መታቀዱም ተገልጿል።

የሸኮ ወረዳ የ350 ሚሊዬን ብር ፕሮጀክት ኮሚቴ ሰብሳቢና የሸኮ ከተማ አስተዳደር ዋና ከንቲባ አቶ ታምራት ምናሴ እንደገለፁት፥ ወረዳው ከዚህ ቀደም በነበሩ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት የልማት ተጠቃሚ ያልነበረ በመሆኑ ይህን ለመፍታት ፕሮጀክት ተቀርፆ እየተተገበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ በባለፉት 2016 በጀት ዓመት የተጀመረ ሲሆን ለ5 ዓመታት የሚቆይ በመሆኑ በመጀመሪያ ዓመት ከ45 ሚሊዬን 350 ሺህ ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ ህብርተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደረጉ የተለያዩ ልማቶች ማከናወኑን የኮሚቴ ሰብሳቢው ተናግረዋል።

በዚህም የሸኮ ከተማ የውስጥ ለውስጥ መንገድ 40 ኪ.ሜ ጥገናና 70 ኪ.ሜ አዲስ ከፈታና እንዲሁም የዳማ ቁ2 ድልድይ ግንባታ ከ20 ሚሊዬን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ ይገኛል ብለዋል።

በፕሮጀክቱ ከታቀዱት መካከል የሸኮ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫና የምስጋና በዓል “ቲካሻ ቤንጊ”፣ የዳማ ቁ 2 ድልድይ ግንባታ፣ የሸኮ ከተማ መልሶ ማልማት እና የባህል ማዕከል ግንባታ ተጠቃሾች እንደሆኑ የኮሚቴ ሰብሳቢው ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ በ2017 በጀት ዓመት በ 2ኛ ዓመቱ ከ112 ሚሊዬን ብር በላይ ለማሰባሰብ የታቀደ ሲሆን በሸኮ ጤና ጣቢያ እየተሰተዋለ ያለውን የግብዓት ዕጥረት ለመፍታት በ500 ሺህ ብር አልተራሳውንድ ማሽን ለመግዛት መታቀዱንም አቶ ታምራት ገልፀዋል።

ህብረተሰቡን የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት በየደረጃ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያደርጉ እንደሚገባ የኮሚቴ ሰብሳቢው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን