ከተሞች ዘመናዊነታቸውን ጠብቀው በአግባቡ እንዲለሙና መጪውን ጊዜ እንዲያገለግሉ ታሰቦ እየተሠራ መሆኑን የፌደራል የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ገለፀ

የአለም ባንክ ካንትሪ ዳይሬክተርና የፌደራል የዘርፉ አካላት የተመራ ልኡክ የጂንካ ከተማ ከ2011 እስከ 2015 ዓ.ም የመሠረተ ልማት ኘሮግራም UIIDP አፈፃፀም ግምገማ መድረክ አካሂዷል፡፡

የጂንካ ከተማ አሰተዳደር ከንቲባ አቶ ሲሳይ ጋልሺ የፌደራል መንግስትና አለም ባንክ ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የከተማውን መሠረተ ልማት ተደራሽነት በማስፋት የቱሪስት መዳረሻ ከተማ ብሎም የሥራ ዕድልና የህዝቡን ተጠቃሚነት ከማሳደግ አንፃር ፕሮግራሙ የጎላ ሚና እንደነበረው ተናግረዋል።

የኣሪ ዞን አስተዳደር ተወካይ አቶ ሳምሶን ግቅሽ በመሠረተ ልማቱ ዘርፍ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ችግሮችን በመለየትና በመስራት ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ገልፀው ተግባሩ ቀጣይነት እንዲኖረውም ጠይቀዋል።

የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ የምስራች ገመዳ የከተማ መሠረተ ልማት ፕሮግራም አፈፃፀም ግምገማ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት ለቀጣይ ሥራ ለመዘጋጀትና ለአለም ባንክም ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።

የፌደራል ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተማ መሠረተ ልማት ሥራ አሰፈፃሚ አቶ ዋኖ ዋኬ በዋናነት የከተሞች መሠረተ ልማት ኘሮግራም UIIDP ዋና አላማ በከተሞች ተቋማዊና መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ኘሮግራም በመሆኑ ባለፉት 15 ዓመታት ሲተገበር የቆየ ሲሆን በኘላን የተቃኘ ከተሞች ዘመናዊነታቸውን ጠብቀው በአግባቡ እንዲለሙና መጪውን ጊዜ እንዲያገለግሉ ታስቦ እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

የአፈፃፀም ግምገማ መድረኩ ተግባራቱን ከሪፖርት በተጨማሪ ያለበትን ደረጃ መመልከትና የማስተዳደር ብቃት፣ ክህሎት፣ የመምራት አቅም ብሎም ተግባሩን ሃሳብ በማዋጣት ለማስቀጠል ያሉ ዝግጅቶችን በመዳሰስ ለቀጣይ ተግባራት ግብዓት የሚወሰድበት ነው ተብሏል።

የአለም ባንክ ካንትሪ ዳይሬክተር ሚስተር ማርቲን ኦንችያ እንደአሉት አለም ባንክ የከተሞች ዕድገትና ለውጥን በመደገፍ ከመንግስት ጋራ በጋራ እየሠራ ያለ ሲሆን ይህንኑም ምልከታ ለማድረግ ያለመ ነው መድረክ አንደሆነ አንስተዋል።

ከመድረኩ መልስ የመሰክ ምልከታ እንደሚደረግም ተመላክቷል፡፡

ዘጋቢ: ከተማ በየነ – ከጂንካ ጣቢያችን