ሀዋሳ፡ መስከረም 13/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በስልጤ ዞን ምስራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ የጆንጎ ልማት ማህበር ከየሪም ልማት ማህበር ጋር በመተባበር አቅም ለሌላቸው ከ1ሺ 7 መቶ በላይ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
“በአቅም ማነስ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው የሚርቁ ህፃናትን እናግዝ” በሚል መሪ ቃል የትምህርት ቁሳቁሶችን ከአከባቢው ተወላጆች እና ባለሃብቶች ማሰባሰብ መቻሉን የገለፁት የጆንጎ ልማትና በጎ አድራጎት ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ሽኩር ሻረፋ ናቸው።
በተለያዩ አማራጮች የሚሰበሰቡ ሀብቶች የማህበረሰቡን ችግር በሚቀርፉ ልማቶች ላይ እንደሚውሉም ገልፀዋል።
ከ800 ደርዘን በላይ ደብተር እና እስክሪፕቶ በማሰባሰብ በ2017 የትምህርት ዘመን አቅም አጥተው ትምህርታቸውን ሊያቋርጡ ይችላሉ በሚል ለተለዩ ከ1ሺህ 7መቶ በላይ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ነው ስራ አስኪያጁ የገለፁት።
ልማት ማህበሩ አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች ያደረገው ድጋፍ የሚያስመሰግን ተግባር ነው ያሉት ደግሞ በርክክቡ ወቅት የተገኙት የወረዳው ምክትል የመንግስት ተጠሪ አቶ አብደላ አህመድ ናቸው።
ይህም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ስብራትን ለመጠገን መንግስት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ከይሩ መሀመድ፥ የልማት ማህበሩን በጎ ተግባር በተማሪዎች ውጤት ለማጀብ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል ።
አንደንድ የልማት ማህበሩ አባላት በሰጡት አስተያያት የማህበረሰቡን ችግር ለመቅረፍ ልማት ማህበሩ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው የተደረገው ድጋፍ እንዳስደሰታቸው በመግለፅ በትምህርታቸው ውጤታማ ለመሆን እንደሚተጉ ተናግረዋል።
የጆንጎ ልማት እና በጎ አድራጎት ማህበር ከዚህ ቀደም ከአርባ ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በትምህርት፣ ጤናና ንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ የአከባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን ማከናወኑ የሚታወስ ነው።
ዘጋቢ፡ ሀጀራ ግርማ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ