330 ሺ ተጋላጭ ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ ህፃናትን በሁለንተናዊ ቀዳማይ ልጅነት ልማት አገልግሎቶች ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 13/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በቀጣይ ጊዜያት 330 ሺ ተጋላጭ ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ ህፃናትን በሁለንተናዊ ቀዳማይ ልጅነት ልማት አገልግሎቶች ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ልማት ማእከል ገለፀ፡፡

የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ልማት ማእከል የቀዳማዊ ልጅነት እና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅኖ ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ  ምክክር በሂልተን ሆቴል እያካሄደ ነው።

መድረኩ በአፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል አዘጋጅነት “የአየር ንብረት ለውጥ በቀዳማይ ልጅነት ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ” በሚል መርህ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።

የማእከሉ  ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ከበደ ወርቁ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት በቀዳማዊ ልጅነት ላይ የሚሰሩ ስራዎች ለልጆች የወደፊት ህይወት ላይ ብቻ ሳይሆን ለአንድ ሀገር እድገት መሰረት የሚጣልበት ነው ብለዋል። ለዚህም  የተመጣጠነ ስነ-ምህዳርን መፍጠር ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ አመላክተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ከሌላው የማህበረሰብ ክፍል በተለየ  ሁኔታ ጉዳቱ ህፃናት ላይ የበረታ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የራሳቸው ጉዳይ አድርገው ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።

ለህፃናት ሁለንተናዊ እድገት በአዲስ አበባ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አመርቂ ውጤት እያስመዘገቡ መምጣታቸውን የጠቆሙት ዶክተር ከበደ ማእከላቸውም ከተማ አስተዳደሩ የጀመረውን የቀዳማዊ ልጅነት ልማት ስራ  ያግዛል ሲሉ ተናግረዋል።

በቀጣይ ጊዜያት 330 ሺ ተጋላጭ ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ ህፃናትን  በሁለንተናዊ ቀዳማይ  ልጅነት ልማት አገልግሎቶች ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል።

አካባቢያችንን መጠበቅ እና ጥሩ ስነ-ምህዳርን መፍጠር ሞራላዊ ግዴታ ነው ያሉት ደግሞ  የማእከሉ ምክትል ስራ አስፈፃሚ መሰረት ዘላለም ናቸው። ስለሆነም ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ሰጪ እርምጃዎችን በመውሰድ ህፃናት ላይ የሚደርሰውን ተፅእኖ ማስቀረት የሁሉም ሀላፊነት ነው ብለዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ልማት ማእከል ዋና ስራ አስፈፃሚ  ከበደ ወርቁ (ዶ/ር)  ጨምሮ ከፍተኛ የፊደራል መንግስት የስራ ሀላፊዎች  እና ከየክልሉ የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ዘጋቢ፡ መሃመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን