የጋሞ ዞን ህዝቦች የቋንቋና ባህል ሲምፖዚየም፣ “ድቡሻና ድቡሻ ዎጋ ለዘላቂ ሰላማችንና ልማታችን” በሚል መሪ ቃል በአርባምንጭ ከተማ በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ይገኛል።
መርሀ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የጋሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙናየ ሞሶሌ የጋሞ ዞን ባህላዊ፣ ሀይማኖታዊ እና ተፈጥሮአዊ መስህቦች የበለፀገ መሆኑን ጠቁመው በተለይ ዱቡሻ ዎጋን ለማልማትና ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ የቱሪዝም ፍሰት እየጨመረና ገቢውም እያደገ መምጣቱን የተናገሩት አቶ ሙናየ የዮ….ማስቃላ በዓል በጋራ የሚከበር ልዩ በዓል በመሆኑ በሁሉም የጋሞ አካባቢዎች ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ እየተከበረ ይገኛል ብለዋል።
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባይነህ አበራ በበኩላቸው በጋሞ ብሔረሰብ ዘንድ የ ዮ….ማስቃላ በዓል ሲከበር ለሰው ልጆች ብቻም ሳይሆን ለእንስሳትና አዕዋፍት ፍሰሀ ይሆናል ብለዋል።
በተለያዩ አጋጣሚዎች የተጣሉ እርቀ-ሰላም አውርደው፣ የተራራቁ ዘመድ አዝማድ ተሰባስበው በፍቅርና በአንድነት የሚያከብሩት በዓል እንደሆነ አውስተው በራሳቸው ቀለም በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከልም እንደሚጠቀስ አስረድተዋል።
በዓሉ ቂምና በቀል የሚቀርበት፣ የሰላም፣ የደስታና የአብሮነት በዓል በመሆኑ የሰላምና የመቻቻል ባህላችንን ለማጎልበት በጋራ መረባረብ ይጠበቅብናል ሲሉ አሳስበዋል አቶ አባይነህ።
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ተወካይና የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ወገኔ ብዙነህ ኢትዮጵያውያን በስነ-ልቦና በታሪክ የተሳሰርን ህዝቦች ነን ብለው በዓሉ የክረምቱ ጭጋግ አልፎ አዲስ ተስፋ የሚፈነጥቅበት ሰላማዊ በዓል ነው ሲሉ ገልፀዋል።
የጋሞ ህዝብ የሚያከብረው የዮ….ማስቃላ በዓል ለዘላቂ ሰላምና አንድነት መጠናከር፣ ለፍቅርና ህዝብ ለህዝብ ትስስር ፋይዳው ከፍተኛ በመሆኑ የክልሉ መንግስት በዓሉን ለማልማት እና ለማበልፀግ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የጋሞ ዞን ህዝቦች የቋንቋና ባህል ሲምፖዚየም፣ “ድቡሻና ድቡሻ ዎጋን አስመልክቶ ጥናታዊ ፅሁፍ የቀረበ ሲሆን የዱቡሻ ወጋ ሰላማዊና ለእውነት የሚወግን በመሆኑ ማበልፀግና ማልማት እንደሚገባ የሲምፖዚየሙ ተሳታፊዎች ሀሳብ ሰንዝረዋል።
በሲምፖዚየሙ በክልሉ የሚገኙ ዞኖች የዮ…ማስቃላ በዓልን አስመልክተው ለጋሞ ህዝብ የተለያዩ ስጦታዎችን አበርክተዋል።
ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ