የዘንድሮው የማሽቃሬ ባሮ አካል የሆነው የካፈቾ፣ የናይ እና የጻራ ብሔረሰቦች የባህልና ቋንቋ ሲምፖዚዬም በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው

ስምፖዚዬሙ በሀገር ሽማግሌዎችና በንጉስ ኮላ ዎችዎቺ ምርቃት ነው የተጀመረው፡፡

የብሔረሰቦቹ የቋንቋ፣ የታሪክና የባህል ልማት የደረሰበትን ደረጃ መገምገምና በግምገማው መሠረት የሚጎለብቱበትን አቅጣጫ ማሳየት የሲምፖዚዬሙ ዋና ዓላማ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ከዚህ ቀደም በብሔረሰቦቹ ቋንቋዎች ላይ በርካታ ሥራዎች የተሰሩ ሲሆን፤ የተስተዋሉ ጉድለቶችን ለይቶ ለማረም ይህ ሲምፖዚዬም ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ፤ የካፈቾ ብሔር ዘመን መለወጫ ከ1887 ዓመተ-ምህረት ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይከበር መቆየቱን አንስተዋል።

በዓሉ ዳግም እንዲከበር ከ1983 ዓመተ-ምህረት በኋላ የተገኘው ዕድል ለብሔሰቡ ባህልና ቋንቋ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ቆይቷል ብለዋል።

በዚህም የካፊ ኖኖ ቋንቋ ከ1987 ዓመተ-ምህረት በኋላ የትምህርት ቋንቋ በመሆን መሰጠት ጀምሮ አሁን ላይ እስከ መጀመሪያ ድግሪ ደረጃ መድረሱን ጠቁመዋል።

ካፊ ኖኖ ከ2002 ዓመተ-ምህረት ጀምሮ የስራ ቋንቋ በመሆን አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው።

ለቋንቋው ዕድገት የበኩላቸውን ሚና የተወጡ አካላትን አመስግነው፤ አሁን ቋንቋውን የተሻለ ደረጃ ላይ በማድረስ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ የመጀመሪያው የቋንቋ ሲምፖዚዬም ከተካሄደበት ከ1998 ዓመተ-ምህረት ጀምሮ ባለፉት 30 ዓመታት የመጡ ለውጦች እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ሁለተኛው የቋንቋ ሲምፖዚዬም መሆኑንም ገልጸዋል።

በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የካፌቾ፣ ናይና ጻራ ብሔረሰቦች የባህልና ቋንቋ ሲምፖዚዬም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ጀኔራል አስራት ደኔሮ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቆጭቶ እና ከተለያዩ አካባቢዎች የተገኙ የብሔሩ ተወላጆችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ነው።

ዘጋቢ ፡ አሰግድ ሣህሌ-ከቦንጋ ቅርንጫፍ ጣቢያ