ሀዋሳ፡ መስከረም 11/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ነጋዴ ሴቶች ማህበር ዘርፍ ምክር ቤት ሀገር ዐቀፍ ንግድ ትርዒትና ባዛር “ያሆዴ ኤክስፖ 2017” እና የማህበሩ የምስረታ ፕሮግራም በክልሉ ሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።
ሰሞኑን ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪና የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ለነበሩ ለፕሮፈሰር በየነ ጴጤጥሮስ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን በመግለጽ ነው መርኃ-ግብሩ የተጀመረው።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ነጋዴ ሴቶች ማህበር ፕሬዝደንት ወ/ሮ ምህረት ተስፋዬ በመክፈቻ ንግግራቸው ወቅት እንደገለፁት፤ የነጋዴ ሴቶች ማህበር በአዋጅ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ካሉ የዘርፉ አካላት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከማስቻል ባሻገር የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማጎልበት ለሀገሪቱ የጋራ ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡ ምቹ አጋጣሚ የፈጠረ ነው።
መርኃ-ግብሩ በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን በሀገር ሰርቶ ማደግና መለወጥ እንደሚቻል ያሳየ ነው ብለዋል።
የሆሳዕና ከተማ ከንቲባ አቶ ዳዊት ጡምደዶ በበኩላቸው በሀገራችን የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ታሳቢ በማድረግ እንደሀገር እየተተገበረ የሚገኘው ከሰንበት እስከ ሰንበት ገበያ በከተማው እንደሚገኝ ጠቁመው በንግዱ ዘርፍ ህገ-ወጥ የንግድ ስርዓት እንዳይፈጠር ከባለድርሻ አካላት በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
በከተማው ለክልሉ ሴቶች ነጋዴ ማህበራት ለጽ/ቤት የሚሆን ቢሮ ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ከንቲባው ቀጣይ ከቦታ ዝግጅት ጀምሮ ለማህበሩ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ይሰራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ፕሬዝደንት ወ/ሮ እንግዳዬ እሸቴ በበኩላቸው ማህበሩ የኢኮኖሚን አውታር ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚያደርሱ ቆራጥ ሴቶችን በማፍራት በፊት የነበረን አመለካከት በማስቀረት ሴቶች በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ተግባራትን የማከናወን አቅም እንዳላቸው ያሳየ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ 51 ፐርሰንት ሴቶች ሲሆኑ ከነዚህም ከ35 ፐርሰንት በላይ ነጋዴዎች ቢሆኑም ምቹ ሁኔታ ያልተፈጠረ በመሆኑ ቀጣይ የሴቶችን አቅም በማጠናከር የሌሎችን አካባቢ ተሞክሮ በመቀመር ለተሻለ ውጤት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
ፕሬዝደንቷ አክለውም የንግዱ ማህበረሰብ ግብይቱን በሰለማዊ ሁኔታ በማካሄድ ለሁሉ ዐቀፍ የህብረተሰብ ጥቅም እንዲሰራ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የገበያ ልማትና ግብይት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታደሰ ዋጄቦ፤ ህገወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየወሰድን ባለንበት ወቅት በዓሉ መከበሩ በተለይ ህገ-ወጥ የንግድ ስርዓትን በቅንጅት ለመከላከል ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።
በክልሉ ባለፉት ሁለት ወራት በርካታ የንግድ ስርዓት ክትትል ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመው ሸማቹ ህብረተሰብ በዚህ የበዓል ወቅት ጊዜ ያለፈባቸውን የንግድ እቃዎች ከመሸመትና በበዓል ወቅት ሊፈጠሩ ከሚችሉ የማጭበርበር ተግባራት ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ