ሀዋሳ፡ መስከረም 11/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የእንሰት ተክል በዘመናዊ መንገድ በማቀነባበር የሴቶችንና ወጣቶችን ተጠቃሚነትን ማጎልበት እንደሚገባ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡
“ጆብ ፊት” የተሰኘ ፕሮጀክት በእንሰት ተክል የሴቶችንና ወጣቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችል ፕሮግራም ማስጀመሪያ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ አካሂዷል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ በእንሰት ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያሳየው ልህቀትና ምርምር ከወረቀት ባለፈ የህዝቡን ችግር እየፈታ መቆየቱ ተመላክቷል።
ጆብ ፊት የተሰኘው ፕሮጀክት የደቡብ ኢትዮጵያን ጨምሮ እንሰት አብቃይ አከባቢዎች ላይ እንሰትን በዘመናዊ መንገድ የሚያመርቱ ሴቶችንና ወጣቶችን ማፍራት አላማ አድርጎ የተነሳ ነው።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ አካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አለማየሁ ጩፋሞ እንደተናገሩት ወጣቶች በአሁኑ ወቅት ስራ ለማግኘት ያለባቸውን ተግዳሮት ለመቅረፍ የእንሰት መስሪያ ማሽኖችን ከማምረት ጀምሮ የእንሰት ውጤቶችን በማቅረብ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ያግዛል።
በይበልጥ ከእንሰት ምርት ጋር ተያይዞ ሴቶች ከፍተኛ ቁርኝት እንዳላቸው ያስታወሱት ዶ/ር አለማየሁ ምርቱን ለማምረት በባህላዊ መንገድ ማዘጋጀት ለሴቶች ከባድ ፈተና ሆኖ ዘልቋልም ብለዋል።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ሀሳብ አመንጪነት ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለወጣቱ የስራ ዕድል በመፍጠር ፋና ወጊ እንዲሆኑ ይጠበቃል ብለዋል።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ የምርምርና ማህበረሰብ ጉድኚት ም/ፕሬዚዳንት ተባባሪ ፕሮፌሰር በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው የእንሰት ምርት ለጤና የሚሰጠውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚመጥነው ስራ እንዳልተሠራ ጠቁመው፥ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ በዘርፉ ያካሄዳቸውን ጥናትና ምርምር ወደ ተግባር እየቀየረ መሆኑ ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።
በይበልጥ የእንሰት ምርትን በስፋት ማምረትና የገበያውን ፍላጎት ማሟላት ሴቶችና ወጣቶችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መጥቀም እንደሆነም አመላክተዋል።
ከ1 ሺህ 500 በላይ ለሚደርሱ ወጣቶች የስራ ዕድልን ይፈጥራል የተባለለት ይህ ፕሮግራም በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በሲዳማና በማዕከላዊ ክልል እንደሚተገበር ያስረዱት ደግሞ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ወንደሰን ጀሬኔ ናቸው።
በይበልጥ የእንሰት ምርት ለተለያዩ የምግብ አይነቶች ከመዋሉም በዘለለ ለተለያዩ ቴክኖሎጂ በመዋል በአለም ገበያ ተፈላጊነቱ እስኪጨምር ድረስ መስራት ይጠበቃልም ብለዋል።
በፕሮጀክቱ ይፋዊ ስራ ማስጀመሪያ መድረክ ላይ ፕሮጀክቱ ከሚተገበርባቸው ሶስት ክልሎች፣ ከኢፌደሪ ግብርና ሚኒስቴርና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል።
ዘጋቢ: በኃይሉ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ