ቢሮው በኣሪ ዞን በባካዳውላ ኣሪ ወረዳ የአንድ አቅመ ደካማ መኖሪያ ቤት ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃግብር አካሄደ

ሀዋሳ፡ መስከረም 10/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ በክልሉ የአረጋውያንና የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታ እያካሄደ መሆኑን አስታወቋል።

የባካ ዳውላ ኣሪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ባሊ ወረዳው ለአቅመ ደካሞችና አረጋዊያን በርካታ ቤቶችን ገንብቶ ማስረከቡን ገልፀው ተግባሩ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ገልጸዋል።

የኣሪ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ስመኝ ተስፋዬ ለአረጋዊያንና አቅመ ደካሞች የሚደረገው በጎ ሥራ ከፈጣሪ ዘንድ በረከት ያለው ነው ብለዋል።

የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር በመገንዘብ በጎ ሥራን ማድረግ መልካም እሴት ሆኖ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊና የፕሮግራሞች ዘርፍ ሀላፊ አቶ መና መኩሪያ የክልሉ ጤና ቢሮ በክረምቱ ነፃ ምርመራና ህክምና አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር በጤናው ዘርፍ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በባካ ዳውላ አሪ ወረዳ መኖሪያ ቤት የሚገነባላቸው አቅመ ደካማ እናት ከ300 ሺህ ብር ወጪ እንደሚደረግበትም ተናግረዋል፡፡

እንደ ክልል ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ቢሮው መድቦ በክልሉ ስር በሚገኙ መዋቅሮች ለአረጋውያንና አቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤት ግንባታ እያካሄደ መሆኑን አቶ መና አስረድተዋል።

ቤት የሚገነባላቸው እናትም ከዚህ በፊት ተቸግረው ይኖሩ እንደነበር ገልፀው ከዚህ ማህበራዊ ችግር እንዲላቀቁ ድጋፍ ያደረገውን የክልሉን ጤና ቢሮ አመስግነዋል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን