ከ178 ሺህ ኩንታል በላይ የስኳር ድንች ምርት እንደሚሰበሰብ የኮሬ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ

ሀዋሳ፡ መስከረም 10/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በባለፈው የበልግ ወቅት 669 ሄክታር መሬት በስኳር ድንች የተሸፈነ ሲሆን 178 ሺህ 354 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ የኮሬ ዞን ግብርና መምሪያ የሆርቲካልቸር ልማትና ጥበቃ ዳሬክቶሬት አስታውቋል።

በኮሬ ዞን ግብርና መምሪያ የሆርቲካልቸር ልማትና ጥበቃ ዳሬክቶሬት ወ/ሮ ይደነቁ በዛብህ እንደገለጹት፥ የስኳር ድንች ተፈላጊነቱም እየጨመረ በመምጣቱ ምርቱ ወደ አጎራባች ዞኖችና ክልል እየተጫነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አክለውም ወይዘሮ ይደነቁ የተለያዩ ንጥረነገር ያለው ብርቱካናማ የስኳር ድንች ዝርያ የተወሰኑ ቀበሌያት ላይ ማስፋፋት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ ከጋሙሌና ቆቦ ቀበሌያት ያነጋገርናቸው አርሶ አደር ደግፌ ደያሶ እና ወጣት ወለጋ ወረደ፥ ስኳር ድንች የተከሉ ሲሆኑ ዘንድሮ በቂ ዝናብ በመኖሩ ከ100 ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ስኳር ድንች በባህሪው ተኮትኩቶ ሀረግ ካወጣ በአረም የማያስቸግር እንዲሁም ያለ ማጣፈጫ የሚቀርብ በመሆኑ ለአመጋገብም ምቹ ነው ብለዋል።

የስኳር ድንች የተለያዩ የጤና ጠቀሜታዎች እንዳሉትም ይነገራል።

ዘጋቢ: ምርጫ መላኩ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን