ሀዋሳ፡ መስከረም 10/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የመስቀል በዓል በክልሉ የሚገኙ የብሄር ብሔረሰቦች ባህል፣ እሴትና ወጎች ለማልማትና ለማስተዋወቅ ምቹ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
በዓሉ የህዝቦች የእርስ በርስ ትስስርንና ቁርኝትን እንዲሁም ፍቅርና መተሳሰብን የሚያጠናክር መሆኑም ተገልጿል።
በመስቀል በዓል ወቅት ከ3 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች በማስተናገድ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በክልሉ ኢኮኖሚ ውስጥ ይንቀሳቀሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተመላክቷል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትልና የባህል ዘርፍ ሀላፊ አቶ ደግነህ ቦጋለ ከወልቂጤ ኤፍ ኤም 89.2 ሬዲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፥ በመስከረም ወር በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ብሄር ብሔረሰቦች የመስቀልና የዘመን መለወጫ በዓል ወቅት በመሆኑ ሰፊ ዝግጅት በማድረግ በደማቅ ሁኔታ ይከበራል።
በክልሉ ወሩን የበዓል ፌስቲቫል ሆኖ እንዲከበር ሰነድ ተዘጋጅቶ በክልል ደረጃ ከዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ጋር ሰፊ ምክክር መደረጉን የጠቆሙት አቶ ደግነህ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ባዛርና ሲምፖዚየም እንዲሁም ፌስቲቫሎችን በማዘጋጀት እየተከበረ ይገኛል ነው ያሉት።
የመስቀል በዓል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ያሉት አቶ ደግነህ በበዓሉ ህዝቦች በጋራ ሲያከብሩ የእርስ በርስ ትስስርንና ቁርኝትን እንዲሁም ፍቅርና መተሳሰብን እንደምያጠናክር አመላክተዋል።
በዓሉ በክልሉ የሚገኙ የብሄር ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓል ጭምር በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ያሉት ምክትል ሀላፊዉ፥ በዓሉ የተጣላ የሚታረቅበት፣ ቂምና ቁርሾን ትቶ በፍቅርና በይቅርታ ራስን በማደስ አዲስ ተሰፋና ዕቅድ የሚሰነቅበት ነው።
በመስቀል በዓል ወቅት ከ3 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች በማስተናገድ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በክልሉ ኢኮኖሚ ውስጥ ይንቀሳቀሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት ኃላፊው ለዚህም ሆቴሎችና የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
በበዓሉ ወቅት በየብሔረሰቡ ያሉ ባህሎች፣ እሴቶችና ወጎችን ለማልማትና ለማስተዋወቅ ምቹ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ያስታወቁት አቶ ደግነህ ለበዓሉ የተለያዩ የባህል አልባሳት፣ ባህሉን የሚገልፁ የዕደ ጥበብ ውጤቶች ተዘጋጅተው ለገበያ ይቀርባሉ ብለዋል።
በመሆኑም በክልሉ በሚገኙ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በባህል አልባሳትና በሌሎች የዕደ ጥበብ ውጤቶች የተደራጁ ማህበራት የገበያ ትስስር እደሚፈጥር ገልፀው በዚህም በክልሉ ባሉ መዋቅሮቾ ከ 3 ሚሊዮን 850 ሺ በላይ ብር ከዕደ ጥበብ ምርት ሽያጭ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
በዓሉ በክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጭ የሚገኙ ሰዎች በዓሉን ተገኝተው እንዲያከብሩ ጥሪ በማቅረብ በ2017 ዓ/ም የስራ ዘመን ክልሉ ውስጥ ያሉ የባህልና ቱሪዝም ሀብቶችን ይበልጥ በማልማት የዜጎች ተጠቃሚነትን የሚረጋገጥበት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ተዘራ በቀለ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ