“ውጤቶች ተመዝግበዋል” – አቶ እንዳሻው ጣሰው

በመለሰች ዘለቀ

ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በኢትዮጵያ ማዕከላዊ አቅጣጫ የሚገኝ ክልል ነው፡፡ በ7 ዞኖች፣ በ3 ልዩ ወረዳዎች፣ በ29 የከተማ አስተዳደሮችና በ50 ወረዳዎችና በ1ሺህ 319 ቀበሌዎች የተዋቀረ ክልል ነው፡፡ ክልሎች 10 ብሄረሰቦችን በማቀፍ በህዝቦች የጋራ ስምምነት የተመሰረተ ክልል ነው፡፡ አስሩ ብሄረሰቦች የጋራ የሚያደርጓቸው በርካታ እሴቶች አሏቸው፡፡ ለአብነትም ባህላዊ የቤት አሰራር፣ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት፣ የእንሰት ምርት አጠቃቀምና፣ ሌሎች የጋራ እሴቶች ያመሳስሏቸዋል፡፡

የክልሉ ይፋዊ ምስረታ “አዲስ ምዕራፍ፣ አዲስ ተስፋ፣ ለአዲስ ክልል”፥ በሚል መሪ ቃል ጥቅምት 17/2016 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡ የክልሉ 1ኛ አመት የምስረታ በዓል አዲስ ምዕራፍ፣ የወል እሴት ወደ ማስፈንጠር ከፍታ በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች በሆሳዕና ከተማ ሰሞኑን ተከብሯል፡፡ በበዓሉ ላይ ክልሉ በአንድ አመት ጉዞ የተመዘገቡ ሁነቶችን የሚያሳዩ የፎቶ አውደ ርዕይና ዘጋቢ ፍልም ለእይታ ቀርቧል፡፡

በበዓሉ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ እንዳሻው ጣሰው እንዳሉት ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የክልሉ ብሄረሰቦች የጋራ እሴቶቻቸውን በማጠናከር የጋራ ዕጣ ፋንታቸውን ብሩህ ለማድረግ ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም መመስረቱ ይታወሳል፡፡ ክልሉ ተመስርቶ ወደ ስራ ሲገባ በርካታ ፈተናዎች ነበሩ፡፡ ለአብነትም የሰላምና የጸጥታ ጉዳይ፣ የማህበራዊ ሚዲያዎች መበራከት፣ የማዳበሪያ እዳና አቅርቦት ችግር፣ የሰራተኞች ደሞዝ አለመከፈል፣ የመሬት ወረራ፣ ያልፈቀዱ ኬላዎች፣ ህገ-ወጥ ንግድ የማዋቅር ጥያቄና 5.5 ሚሊዮን ብር በላይ እዳ እንዲሁም ጎሰኝነት የባላይነት የያዙበት ክልል እንደነበረ ርዕሰ መስተዳደሩ ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ችግሮች በበቂ ሁኔታ ለመመከት ህዝቡን በማወያያትና ለሰላምና ፀጥታ ስራዎች ቅድሚያ በመስጠት በተሰራው ስራ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

በተለይም ግብርና ፣ገቢ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ንግድና ኢንቨስትሜንት፣ የስራ ዕድል ፈጠራና በመሰረተ ልማት ስራዎች ላይ ርብርብ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ተገቢው የአመራር ስምሪትና ምደባ በመስጠት፣ወቅታዊ ሪፖርትና የመስክ ጉብኝት በማቀናጀት ያለእረፍት በመስራት በሁሉም መስክ ውጤት መመዝገቡን አቶ እንዳሸው ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በአንድ አመት ጉዞ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት የሚያስቃኙ ሰነዶች በምሁራን ቀርበው ወይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ የርዕሰ መስተዳድሩ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ ረዳት ፕሮፌሰር አንተነህ መሎ የክልሉን የአንድ አመት የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች በሚመለከት ሰነድ አቅርበዋል፡፡

ከክልሉ ምስረታ ጀምሮ የተካሄዱ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ጥበብን በተላበሰ መንገድ ሽግግር ለመፍጠር የተደረጉ ቅንጅቶችና የአመራር ውህደት፣ለሰላምና ጸጥታ የተሰጠው ልዩ ትኩረት፣ ተከታታይነትና ወጥነት ያላቸው የተግባር ክትትልና ግምገማ ሂደቶች፣ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማረጋገጥ የተደረጉ ጥረቶች፣ ተከታታይ ህዝባዊ ውይይቶች በጥንካሬ የሚነሱ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።

የሳላምና ጸጥታ ከማረጋገጥ ረገድ ከክልሉ ተወላጅችና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተከታታይ ውይይችን በመደረጉ በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች የተረጋጋና ሰላም የሰፈነበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

የትምህርት ስብራትን ለመጠገን በርካታ ተግባራቶች የጠከናወኑ ሲሆን በህብረተሰብ ንቅናቄ በአይነት፣ በጉልበት፣ በእውቀትና በጥሬ ገንዘብ 1.1 ቢሊዮን ብር በተሰበሰበው ገቢ የትምህርት ቤቶችን የመሰረተ ልማት ማሻሸያ መከናወናቸውን አብራርቷል፡፡

በትምህርት ዘመኑ በደበኛ ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ከወሰዱ 44 ከመቶ ተማሪዎች 50 በመቶና በላይ ውጤት አምጥቷል፡፡ ይህም ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር የ138 በመቶ እድገት የታየበት እንደሆነ ነው ያመለከቱት፡፡ አንድ መጽሃፍ ለአንድ ተማሪ በሚል መሪ ቃል 323 ሚሊዮን ብር ሀብት በማሰባሰብ 264ሺህ 797 መጽሀፍት ታትመው ለተማሪዎች እንዲደርሱ ተደርጓል፡፡

በጤና ዘርፍም በተለያዩ መስኮች ውጤት መመዝገቡን ተመላክቷል፡፡ ለአብነትም የጤና መድን ስርዓቱ ለጤናው ሴክተር ምንጭ እንደመሆኑ መጠን 577 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ከአባላት መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ይህም ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ማሳደግ የተቻለበት አመት ነበር፡፡

በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተተገበሩ አዳዲስ ሀሳቦችና የአሰራር ስልቶች ውጤታማ እንደነበሩ በጥናቱ የተመላከተ ሲሆን በተለይም በግብርና “ኢንሼቲቭ” 3.3 ሚሊዮን ችግኝ የተተከለ ሲሆን በርካታ አርሶ አደሮች በፍራፍሬ፣ በአንስሳት ሀብት የዶሮና የወተት መንደሮችን መፍጠር የተቻለበት አመት ነበር፡፡ በተለይም በበጋ መስኖ ስንዴ፣ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት በአመት ከሁለት ጊዜ በላይ ማምረት ባህል እየሆነ መጥቷል፡፡

የሰንበት ገበያዎች መስፋፋት፣ የከተሞችን አሰራር በማዘመን የአገልግሎት አሰጣጥን ለማጎልበት የተደረገው ጥረት እና የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን ለስኬት ለማብቃት እንዲሁም የክልሉን እዳ ለማቃለል ከ5.5 ቢሊዮን እዳ 3 ቢሊዮኑን መክፈል መቻሉ፥ የታየው ቁርጠኝነትም በስኬት የሚነሱ ናቸው ብለዋል።

በቤት አቅርቦት ረገድ በተለይም በማህበር ለተደራጁ ማህበራት የቤት መስሪያ ቦታ ማቅረብ የታቻለ ሲሆን ለ385 ማህበራት ወይም ለ5 ሺህ 156 አባላት የግንባታ ቦታ ማስረከብ የተቻለበት አመት ነበር፡፡

ከኢንቨስትመን ዘርፍ በክልሉ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ያሳዩ ባለሀብቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ 268 ፕሮጄክቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥተው በተመረጡ ዘርፎች ላይ ተሰማርተዋል፡፡ በዚህም 13.4 ቢሊዮን ብር ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ ከስራ እድል ፈጠራ ረገድ ለ46ሺህ 775 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር የተቻለበት አመትም ነበር፡፡

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊል የክልሉ ቀጣይ አቅጣጫዎች በሚል ባቀረቡት ሰነድ ታታሪና ስራ ወዳድ የሆነውን የክልሉ ህዝብ ማስተባበር፣ የንግድ ዘርፍ ክህሎትና የደረጀ ልምድ በአግባቡ መጠቀም፣ የክልሉን የኢንደስትሪና የግብርና ዘርፎች አቅም ማጎልበት ላይ የበለጠ ትኩረት ቢሰጥ የክልሉን ጅምር ተስፋ ጽኑ መሰረት ማስያዝ እንደሚቻል ተናግረዋል።

ክልሉ በርካታ ጸጋዎች እንዳሉት ያነሱት ዶ/ር ፋሪስ ለማዕከል ያለውን ቅርበት፣ ምቹ የግብርና ስነ ምህዳር፣ የኢንዱስትሪ አቅምና የንግድ ዘርፍ ስኬታማ የህዝብ ተሞክሮ እንዲሁም የሰለጠነና የተማረ የሰው ሃይል አቀናጅቶ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል።

በቀረቡ ሰነዶች ላይ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎችና አስተያያቶች ተነስተዋል፡፡ በፓናል ውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ የፌደራልና የአዲስ አበባ ከተማ አመራሮች የክልሉ አመራር በአጭር ጊዜ ውስጥ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ፈጥሮ ክልሉን የመራበት መንገድ የሚደነቅ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የቀድሞ የደ/ብ/ብ/ህ/ክ ርዕሰ መስተዳድርና የአሁኑ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ርስቱ ይርዳው እንዳሉት የክልሉ አመራር ውህደት ፈጥሮ እንደ ነባር ክልል የመራበት መንገድ የሚደነቅ ነው። ለዚህም ያስመዘገባቸው ስኬቶች አመላካች መሆናቸውን ጠቁመው ይህ ስኬት ቀጣይነት ይኖረው ዘንድ የውስጥ ገቢን ማሳደግ፣የህዝብ አቅምን አሟጦ መጠቀም፣ምቹ ሁኔታዎችንና እድሎችን ማስፋት ላይ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር ታደለ ቡራቃ በበኩላቸው ክልሉ ባስመዘገባቸው ስኬቶች ላይ ሀብትን በአግባቡ የማስተዳደር፣የወል እሴትና የጋራ ራዕይ የመንደፍ ተግባርን በማጠናከር የተገኙ ውጤቶችን ቀጣይነት እንዲያረጋግጥ በቁርጠኝነት መስራት ያስፈልጋል።

የክልሉ አመራር ቁርጠኝነትና ታታሪነት አዲስ አደረጃጀቱንና ሽግግሩን በብቃት እንዲመራ ማስቻሉን ጠቁመው በቀጣይ የህዝቡን ልምድና ተሞክሮ፣ የክልሉንም ባለሀብት፥ የሰው ሃይል የልማት አቅም መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ ሰላምን ማስፈንና ቀልጣፋ የአሰራር ስርኣት መዘርጋት ብሎም ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥን ማስፈን ይገባል፤ ክልሉ ከዩኒቨርስቲዎች ጋር ያለውን ቁርኝት ማጠናከርና የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን ለዚህ ደግሞ ጠንካራ ሪፎርም ማድረግ እንደሚጠበቅበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።