ለወንጀል ድርጊት አመቺ የሆኑ ቦታዎችን በመቃኘት በአካባቢው ያለውን ሠላም በዘላቂነት ለማስቀጠል እየተሠራ ነው – የዲላ ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት

ሀዋሳ፡ መስከረም 09/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለወንጀል ድርጊት አመቺ የሆኑ ቦታዎችን በመቃኘት በአካባቢው ያለውን ሠላም በዘላቂነት ለማስቀጠል እየሠራ መሆኑን በጌዴኦ ዞን የዲላ ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡

ጽ/ቤቱ በዲላ ከተማ ከ5ቱ ቀበሌያት እና ቀጠና ለተመረጡ ገለልተኛ አማካሪ ቡድንና ማህበረሰብ ደኀንነት ቅኝት ዙሪያ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

ሥልጠናው በማህበረሰብ ውስጥ የሚስተዋሉ ወንጀሎችን ለመቅረፍ ፋይዳ አለው ተብሏል፡፡

የዲላ ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ቡድን መሪ ምክትል ኮማንደር አበባ አክሊሉ፤ ለሥልጠናው የተዘጋጀ ጽሑፍ ባቀረቡበት ወቅት ወንጀል በማህበረሰብ የሚፈጸም መሆኑን ጠቅሰው ወንጀለኛው በማህበረሰብ ውስጥ እንደሚሰገሰግ ተናግረዋል፡፡

ወንጀለኛን ህብረተሰቡ አጋልጦ እንዲሰጥና የለመደውን ከፖሊስ ጋር ተቀናጅቶ የመስራት ባህል አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ለማድረግ ሥልጠናው አስፈላጊ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በሰነዱ ዙሪያ የውይይት መድረኩን የመሩት የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዲቪዥን ምክትል ኢንስፔክተር ቦጋለ ገመዴ፤ ከተማው ሰው በሠላም ወጥቶ የሚገባበት በመሆኑ በቀሪ ጉዳዮች በመወያየትና ማህበረሰብ ደህንነት ፓትሮል ቅኝት በማጠናከርና በሰነድ የቀረቡ ሀሳቦችን በተግባር ለማዋል መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የቅድሚያ ወንጀሎችን ለመከላከል ከፖሊስ መዋቅር ጀምሮ ማህበረሰቡን በማጠናከር እንደሚሠራም ገልፀዋል፡፡

የዲላ ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት ዋና አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር እድገት ህርባዬ የሚፈጠሩ ወንጀሎችን ለመከላከል የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ እንዳለ ሆኖ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በመሰራቱ በከተማው ይፈጸም የነበረው እየቀነሰ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡

የከተማው ሠላም የሁላችንም ሠላም መሆኑን በመገንዘብ አሁን እየተስተዋሉ ያሉ ወንጀሎችን በመከላከልና ለወንጀል ድርጊት አመቺ የሆኑ ሁኔታዎችን በመለየት ለዘላቂ ሠላም በተደራጀ መልኩ መሠራት እንዳለበት አንስተዋል፡፡

በከተማው በሰዋራ ቦታዎች የሚፈፀሙ የተንቀሳቃሽ ስልክ ነጠቃና ስሮቆቶች በመኖራቸው አሁንም የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አዛዡ ተናግረዋል፡፡

የዲላ ከተማ ሠላምና ጸጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ ከበደ ሠላም በጸጥታ ኃይል ብቻ እውን ስለማይሆን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ወንጀልን በመከላከል ሥራ መረባረብ አለባቸው ብለዋል፡፡

የሥልጠናው ተካፋዮችም የወንጀል አዝማሚያዎችንና የስጋት አካባቢዎችን በመለየት ጠንከር ባለ መልኩ መሠራት እንዳለበት በመጠቆም ከፖሊስ ጎን በመቆም የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡ እምነት ሽፈራው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን