የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተቀርፈው ህብረተሰቡ ተገቢ አገልግሎት እንዲያገኝ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 08/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተቀርፈው ህብረተሰቡ ተገቢ አገልግሎት እንዲያገኙ መስራት እንደሚገባ በጌዴኦ ዞን የቡሌ ወረዳ ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡

እንደ ሀገር በተደጋጋሚ እየተመዘገበ ባለው የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል በወረዳው በከፍተኛ ሁኔታ መስተዋሉን የገለጹት የምክር ቤቱ አባላት ለዚህም የክፍለ ጊዜ ብክነት፣ መምህራን በትምህርት ቤቶች አቅራቢያ ባለመኖራቸው ራቅ ካለ ቦታ ተመላልሰው የማስተማርና የዓመቱን ትምህርት በተገቢው ሁኔታ አለማጠናቀቅ የሚጠቀሱ ምክንያቶች በመሆናቸው ትኩረት እንዲሰጥ በአጽንኦት አንስተዋል፡፡

በቡሌ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የመድኃኒት አቅርቦትና ሌሎች ችግሮችን በመፍታት የህብረተሰቡን የአገልግሎት እርካታ ለማሳደግ በቁርጠኝነት መረባረብ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡

የሥራ ሰዓትን ጠብቆ ከመስራት ረገድ በአንዳንድ ተቋማትና ባለሙያዎች የሚታየው ክፍተት መቀረፍ እንዳለበት የጠየቁት የምክርቤቱ አባላት፤ በበጀት ዓመት የተከናወኑ በጎ ሥራዎች እንዳሉ ሆኖ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተቀርፈው ህብረተሰቡ ተገቢ አገልግሎት እንዲያገኝ በቀጣይ በውስንነቶች ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት አለበት ብለዋል፡፡

ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በትምህርት ዘርፍ የተስተዋለውን የውጤት ማሽቆልቆል ችግር ለመቅረፍ መንግሥት የተለያዩ አማራጮችን ወስዶ እየሠራ መሆኑን የተናገሩት የወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ከድር ያሲን በዚህም የትምህርት የግብዓት ችግር ለመፍታት በተለያዩ አካላት ድጋፍ የታተሙ መጻሕፍትን በማሰራጨት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ በራቆ በራሶ በበኩላቸው የወጣቶች መዝናኛ ስፍራ የቁሳቁስ ያለመሟላት፣ የትምህርት ጥራት ችግሮች፣ በግብር አሰባሰብ፣ የሥራ ሰዓት አጠቃቀምና በሌሎች ዘርፎችን የተነሱ ጉዳዮች ትክክለኛ መሆናቸውንና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመመለስ መስራት እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ዋቆ መኮና በበኩላቸው ከአባላቱ የተነሱ ጉዳዮችን በቃል ከሚሰጠው ምላሽ ይልቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተግባር ለመመለስ የዕቅድ አካል አድርጎ መስራትን እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል፡፡

ጉባኤው ለ2017 የተያዘው 256 ሚሊዮን 417ሽህ ብር በላይ በጀትና ሹሜት በማጽደቅ ተጠናቋል፡፡

ዘጋቢ፦ እምነት ሽፈራው -ከይርጋጨፌ ጣቢያችን