ሀዋሳ፡ መስከረም 08/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጉራጊኛ ቋንቋ የሚጻፉ መጽሐፍት ለቋንቋው እድገት፣ መልማት፣ መበልጸግና ወደ ትውልዱ ለማድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ስነ-ጽሁፍ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ካሚል ኑረዲን ገለጹ፡፡
በደራሲ ወንድሙ ብሩ የተደረሰው ”የኰር ስማት” የተሰኘው የጉራጊኛ ልብ ወለድ መጽሐፍ በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ተመርቋል፡፡
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ስነ-ጽሁፍ መምህርና ደራሲ ረዳት ፕሮፌሰር ካሚል ኑረዲን በምረቃው ወቅት እንደተናገሩት ቋንቋን ማሳደጊያ ዋናዉ መንገድ ቋንቋዉን ወደ ስነ-ጽሁፍ ማሳደግ ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጉራጊኛ ቋንቋ የሚጻፉ መጽሀፍት በጥራት፣ በብዛትና ጊዜውን በመዋጀት መሻሻሎች መኖራቸውን ገልጸዉ ቋንቋው፣ ባህሉና ወጉ ላይ የሚጻፉ መጽሐፍት እየተበራከቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህም ለቋንቋው እድገት መልማት መበልጸግና ወደ ትውልዱ ለማድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጹት ረዳት ፕሮፌሰር ካሚል፤ እየተጻፉ ያሉ መጽሐፍትን የማንበብ ልምድ መዳበር እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
”የኰር ስማት” የልብወለድ ይዘት ኖሮት ታሪክን፣ ባህል፣ ማንነትና በሀገር ግንባታ የጉራጌን ድርሻ የሚያወሳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የቋንቋ ጥናትና ልማት አስተባባሪ አቶ ባህሩ ሊላጋ በበኩላቸው ጉራጌ በባህሉ በርካታ አስተማሪ የሆኑ እሴቶች ያሉት ቢሆንም በቋንቋዉ ብዙም ሳይሰራ እንደቆየና አሁን ተስፋ የሚሰጥ ነገር እየታየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዘርፉ ጸሐፍት እየበዙ የትምህርትና የሚዲያ ቋንቋ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመው የደራሲ ወንድሙ ብሩ መጽሐፍ ባህሉን የሚያስተዋዉቅና ለጉራጊኛ ልብ ወለድ መሰረት የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
የጉራጊኛ የፊደል ገበታን ለማስተዋወቅ ፋይዳዉ ከፍተኛ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የመጽሐፉ ደራሲ ወንድሙ ብሩ ”የኰር ስማት” በእዉነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ልብወለድ መጽሐፍ መሆኑን ጠቅሰው የጉራጌ ሕዝብ ለሀገር ያደረገውን አበርክቶ፣ የጦር ሜዳ ውሎ፣ ፍቅርን የሚዳስስና የወላጆችን መልካም አርአያ፣ አኗኗሩን፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶቹን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በጉራጊኛ ቋንቋ ዙሪያ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች እየተነቃቁ መሆኑን የገለጹት ደራሲው በማንበብ ሀሳብን መለዋወጥ ለትውልድ ማሸጋገርና ጉራጊኛን ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ረዳት የመንግስት ተጠሪ ወ/ሮ መንዚላ አህመድ በወቅቱ እንደተናገሩት ስነ-ጽሑፍ የአንድን ማህበረሰብ ባህል፣ ታሪክና እሴት ወደ ትውልድ ለማሸጋገር ይረዳል፡፡
የእድገት የስልጣኔ ማሳያና ጉራጌን የሚያስተዋዉቅ በመሆኑ በዘርፉ የሚጻፉ መጽሐፍትን በመግዛት ማበረታታት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የከተማዉ ባህልና ቱሪዝም ፅ/ቤት ኃላፊ ወይዘሪት ንግስት ገብሬ በበኩላቸው ደራሲ ወንድሙ ከዚህ ቀደም ጋዝ ተምዝማዝ፣ የዳነራ ወሬት አሁን ደሞ ”የኰር ስማት” መጻፋቸው ቋንቋውን ለማልማት ጉልህ ድርሻ እየተወጡ መሆኑን ገልፀው መጽሐፉ ተደራሽ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ፅህፈት ቤቱም በቤተ መጽሐፍትና በትምህርት ቤቶች ተደራሽ እንደሚያደርግ ጠቁመው ቋንቋው እንዲለማ ህብረተሰቡ ደራሲውን ማበረታታት እና ማንበብ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
በምረቃዉ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የከተማዉ የመንግስት የስራ ሀላፊዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ኄኖክ ተክሌ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ