በቢሮው የ Redd plus ማስተባበሪያ ዩኒት ቴክኒክ ኮሚቴ በዳውሮ ዞን በፕሮግራሙ በተሰሩ ስራዎች ዙሪያ የመስክ ምልከታ ተካሂዷል።
የክልሉ EEDD+ ማስተባበርያ ዩኒት አስተባባሪ ዶ/ር የሪቾ ብርሐኑ፤ በፕሮጀክቱ ማህበረሰቡ የደን ልማትን እየጠበቁ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል በርካታ ተግባራት ስለመፈፀማቸው አብራርተዋል።
በዚህም በዳውሮ ዞን ከ6 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ከ47 ሺህ 4 መቶ በላይ ሄክታር የተፈጥሮና ሰዉ ሰራሽ ደን ይዞታዎችን በማልማት ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑም ተጠቁሟል።
የክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለዉጥ ቢሮ ምትክል ኃላፊ አቶ ደምሴ ደንቦ፤ በደን ልማት የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የደን ልማት አልምተዉ የአካባቢውን ስነ-ምህዳር ከማስጠበቁም በተጨማር እነሱም የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል ነዉ ያሉት።
የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የእርዳታ ብድር ፕሮግራሞችና የመንግስት ሀብት ዳይሬክተር አቶ ታምራት ታደሰ በበኩላቸው፤ በክልሉ ከ81 ሚልየን ብር በላይ በጀት በዘርፉ ከፕሮጀክቱ ተመድቦ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል። ይህም በጀት ለታለመለት ዓላማ መዋል ያለመዋሉን እስከ ቀበሌ ወርደው እያረጋገጡ መሆኑን ተናግረዋል።
የዞኑ ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ መምሪያ ኃላፊ አቶ በተላ በየነም፤ ዞኑ ሰፋፊ የተፈጥሮና ሰዉ ሰራሽ ደን የሚገኝበት አካባቢ ቢሆንም ከዘርፉ ተጠቃሚ ሳይሆን መቆየቱን ተናግረዋል። አሁን ግን REDD plus በሰራው ስራ ከዘርፉ ተጠቃሚነት እየጎለበተ መጥቷል ነዉ ያሉት።
በሂደቱ ደን አካባቢ በሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሲስተዋል የነበረውን የግንዛቤ ክፍተት ለመፍታት ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተሰራው ስራ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉም ተጠቁሟል።
ዘጋቢ፡ እሸቱ ወርቅነህ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ 120 የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ