በአዲሱ 2017 ዓመት ከአባቶቻችን የተረከብነውን ሉዓላዊ ሀገር የበለጠ አበልጽገን ለልጆቻችን ለማሻገር በአንድነት መትጋት አለብን – የሀገር ሽማግሌዎች

ሀዋሳ፡ መስከረም 07/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአዲሱ 2017 ዓመት ከአባቶቻችን የተረከብነውን ሉዓላዊ ሀገር የበለጠ አበልጽገን ለልጆቻችን ለማሻገር በአንድነት መትጋት አለብን ሲሉ የሀዲያ ዞን የሀገር ሽማግሌዎች ገልጸዋል።

የሀዲያ ዘመን መለወጫ ያሆዴ በዓል በዞኑ ሌሞ ወረዳ ሀይሴ ቀበሌ በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ተከብሯል።

በዞኑ በክልሉና በሀገር፥ ሰላም፣ ልማት እና አንድነት እንዲረጋገጥ የተጉ የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እና የሰላማዊ ፖለቲካ አራማጅ በነበሩ በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ህልፈት የህሊና ፀሎት በማድረግና በባህላዊ ምርቃት ስርዓት ነው የሀገር ሽማግሌዎች ፕሮግራሙን የጀመሩት።

በያሆዴ የሀዲያ ዘመን መለወጫ በዓል ከታደሙ የዞኑ፣ የሀገርና ባህል ሽማግሌዎች መካከል “ሀዲይ ጋራድ” መንገሻ ህቤቦ እና የሌሞ ዳኛ ብርሃኑ ጡሞሮ እንደገለጹት፤ የሀዲያም ሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአዲሱ 2017 ዓመት በአሮጌ አመት ከነበርንበት የክፋት ሀሳብና ተግባር ተላቀን ከአባቶቻችን የተረከብነውን ሉአላዊና ሰላማዊ ሀገር የበለጠ አበልጽገን ለልጆቻችን ለማሻገር በአንድነት መትጋት ያስፈልጋል።

ያሆዴ የሀዲያ ዘመን መለወጫ በዓል ከጥንት ጀምሮ እየተከበረ የመጣ በሀዲያ ብሄር ዘንድ ከሌሎች በዓላት ልዩ ትርጉም ያለው በዓል መሆኑን የባህል ሽማግሌዎቹ ተናግራዋል።

በብሄሩ ዘንድ በዚህ በዓል ከክረምት ጨለማ ወራት ወደ ብርሃን፣ ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲስ ዓመት መሻገርን፣ አዲስ ተስፋና ሀሳብ ማስጀመሪያ፣ ተራርቀው የነበሩ አንድ የሚሆኑበት፣ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ አቅመ ደካሞች የሚረዱበት፣ የዘመን መለወጫና ሌሎች በርካታ ማህበራዊና ባህላዊ ዕሴቶችን የሚያንጸባርቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ለበዓሉ ድምቀት ከጥንትም በተለመደ ስርዓት አባቶች፣ እናቶች፣ ሴትና ወንድ ወጣቶች እያንዳንዳቸው ለረጅም ጊዜ የበኩላቸውን የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያደርጉም በመግለጽ።

ባለፈው 2016 ዓመት በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው ሞትና ግጭት እንዲሁም በሀዲያ ዞን ውስጥም የነበረው የእርስ በርስ ያለመግባባት ችግሮች በአዲሱ ዓመት እንዳይደገሙ ለዞኑ፣ ለክልሉና ለሀገር ሰላምና ልማት በአንድነትና በፍቅር የምንሰራበት ዓመት መሆን አለበት ሲሉም ሽማግሌዎቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በበዓሉ ላይ የተገኙት የሌሞ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ደሚሴ “ያሆዴ” የሀዲያ ዘመን መለወጫ በዓል ከጥንት ጀምሮ እየተከበረ ዛሬ የደረሰ የብሄሩ የማንነት መገለጫና የዘመን መለወጫ በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

በዓሉ በውስጡ በርካታ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ማህበራዊ ዕሴቶችን የያዘ በመሆኑ በዓለም የሳይንስና ትምህርት ድርጅት ዩኔስኮ ላይ ለማስመዝገብ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ከግብ እንዲደርስ በመንግስት በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግና በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የሀዲያ ተወላጆች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ዋና አስተዳዳሪው አቶ ታደለ አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ: ሳሙኤል መንታሞ – ከሆሳዕና ጣቢያችን