ሀዋሳ፡ መስከረም 07/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሀዲያ ብሔር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓል የሠላም፣ የእርቅ፣ የአብሮነትና የመቻቻል በዓል ስለመሆኑ በሀዲያ ዞን የአንሌሞ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።
በዓሉ በዞኑ በአንሌሞ ወረዳ ደረጃ የባህል ሽማግሌዎች፣ የአመራር አካላት እና የአከባቢ ማህበረሰብ በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።
የሀዲያ ብሔር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓል በአንሌሞ ወረዳ ምዕራብ አናሌሞ ቀበሌ የተከበረ ሲሆን የአከባበር ሥነ ሥርዓቱ የተጀመረው በባህል ሽማግሌዎች ምርቃት ነው።
በዓሉ የሚከበርበት ወቅት የክረምት ጊዜ አልፎ የፀደይ ብርሃን የሚፈነጥቅበት ወቅት በመሆኑ ለሀገር ሰላምና ብልጽግና በመሻት ወደ ፈጣሪ ፀሎት የሚቀርብበት መሆኑን ሽማግሌዎቹ አንስተዋል።
የ‘ያሆዴ’ በዓል በማህበረሰቡ ዘንድ ዕርቅ የሚወርድበት፣ በአዲስ መንፈስና ስሜት የመነሳሳት ራዕይ የሚሰንቅበት እንደሆነም ጠቁመዋል።
የሀዲያ ብሔር የበርካታ ባህላዊ ዕሴቶች ባለቤት መሆኑን የገለፁት የአንሌሞ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አማኑኤል አባሞ ከነዚህ ቱባ ባህሎች አንዱ የሆነው የ‘ያሆዴ’ በዓል በአከባቢው በድምቀት የሚከበር በዓል መሆኑን ተናግረዋል ።
የ‘ያሆዴ’ በዓል ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ብሎም በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታውቅ እየተሠራ ነው ብለዋል ።
በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የሀዲያ ዞን ምክትል አስተዳደርና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር በፈቃዱ ወ/ሃና የ‘ያሆዴ’ በዓል በህዝቦች መካከል አብሮነትንና መቻቻልን በማጠናከር ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል ብለዋል፡፡
የ‘ያሆዴ’ በዓል የሀዲያ የዘመን መለወጫ በዓል ከመሆኑም በሻገር ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ ለማህበራዊ መስተጋብርና ለፖለቲካዊ ስርዓት ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ዶ/ር በፈቃዱ አስገንዝበዋል።
ወጣቱ ትውልድ ይህንን ታላቅ ባህላዊ ትውፊት በማስቀጠል እና ሰላምን በማጽናት የትውልድ ቅብብሎሽ አሻራ መጣል ይጠበቅበታልም ብለዋል።
በመጨረሻም ችቦ ለኩሰው የደመራ ስነ ስርዓት በማከናወን የዕለቱ ዝግጅት ተጠናቋል ።
ዘጋቢ: መንግሥቱ ፊጣሞ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
ተማሪዎች በወቅቱ ትምህርት ቤት ቀርበዉ እንዲመዘገቡ ወላጆች የሚጠበቅባቸዉን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ
የተጀመሩ የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሀዲያ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ተናገሩ
በሆሳዕና ከተማ እየተገነባ ያለውን የመንገድና የኮሪደር ልማት ስራ በታቀደው ጊዜ በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ