በግብርናው ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት በልዩ ትኩረት  እየተሠራ  መሆኑ  ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 06/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል ማነቆ የሚሆኑ ችግሮችን ለይቶ መፍታት እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

የወላይታ ዞን ግብርና መምሪያ የ2016 አፈጻጸምና የ2017 ዕቅድ ላይ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጴጥሮስ ወ/ማርያም ግብርና በሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገትና ድህነትን በመቀነስና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

በግብርናው ዘርፍ የተለያዩ ስትራቴጅዎችን በመቀመር በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ ለዉጥ ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት በመደረጉ በዞኑ ተጨባጭ ዉጤት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡

በሆልቲካልቸርና በአዝርት ሰብሎች እያደገ የመጣዉ የምርታማነት መጨመር የምግብ ዋስትናና የስነ ምግብ ችግር፥ የኑሮ ዉድነት ለመቀነስ፣ ኤክስፖርት በመጨመርና ኢምፖርት በመቀነስ የሀገር ኢኮኖሚ ከማሳደግ አንጻር አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በመስኖ የተለያዩ ሰብሎችን የማምረት አቅማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ በመገለጽ ቀጣይ አ/አደሩ አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችን እና ዘመናዊ አተራረስ ዘዴን እንዲጠቀሙ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ በምግብ ራሱን እንዲችል በትንሽ መሬት ብዙ ምርት የሚሰጥ ቴክኖሎጂን መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።

ህገወጥ የቡና ግብይትን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ መስራት እንደሚገባ ያሳሰቡት ዋና አስተዳዳሪው ለዚህም ግብረኃይሉ ልዩ ትኩረት መሰጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ቴክኖሎጂን በአግባቡ በመጠቀም አርሶአደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው የሚሰጣቸው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

መሬት የማይለጠጥ ከሀብት ሁሉ በላይ ዉድ ሀብት ነዉ ያሉት ዋና አስተዳዳሪው መሬትን በአገባቡ ማስተዳደርና መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የወላይታ ዞን ግብርና መምሪያ ም/ኃላፊ አቶ መስፍን መድህን በበኩላቸው የግብርና ሴክተር በዘርፉ የሚስተዋለውን የምርታማነት ማነቆዎችን በመፍታት እና ዘመናዊ ቴክኖሎጅ አጠቃቀምን በማሻሻል በተደረገው ጥረት ተጨባጭ ዉጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

ምርታማነትን በማሳደግ የህብረተሰባችንን የምግብ እና ስነ-ምግብ ዋስትናን በአስተማማኝ ደረጃ ለማሟላት በግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚጠይቅ አመላክተዋል።

ዘጋቢ፡ በቀለች  ጌቾ – ከዋካ  ጣቢያችን