በፈረኦን ደበበ
ጎረቤት የሆኑት ኢትዮጵያና ሶማሊያ ረጅም ታሪክ ያላቸው ሀገራት ናቸው፡፡ ከመልክዓ ምድር ባለፈ የጠበቀ የህዝብ ለህዝብ ትሥሥር አላቸው፡፡ ይህን ታሳቢ በማድረግም ነው ሀገራችን ለሶማሊያ መረጋጋት ዋጋ ስትከፍል የቆየችው፡፡
አሁን በሶማሊያ በኩል እየታዩ ያሉ አዝማሚያዎች ግን፥ ከዚህ መስተጋብር ወጣ ያሉ ናቸው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ዕድገቷን ለማስቀጠል የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ተከትሎ ካላት ሰፊ የባህር ዳርቻ አንዲት ስንዝር እንኳን ለማዋስ ያለመፈለጓ ትዝብት ላይ የሚጥላት ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ጋር ማበሯ የአጉራሽን እጅ ነካሽ ያደርጋታል፡፡
እንደ ሮይተርስ ያሉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀንም ይህንን ሀቅ አስተጋብተውታል። በሶማሊ ላንድ ጉዳይ መንግሥት በውይይት ላይ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ግብጽ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት መፈጸሟ አግባብ አይደለም፡፡ በቱርክ አማካይነት እየተደረገ ያለው ሽምግልና መቋጫ ባላገኘበትና በመጪው መስከረም ወር እንደሚቀጥል ቀጠሮ ተይዞ እያለ ሂደቱን ማበላሸታቸው ያሳዝናል፡፡
ብዙ የውጭ መገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት ከሆነ ግብጽ እስከአሁን ብዙ ቁጥር ያለው ወታደርና ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን በሶማሊያ አስፍራለች፤ በቀጣይ የሚመጡ ወታደሮችና መሣሪያዎች እንዳሉ በመጥቀስ፡፡
ሀገራችን በሉዓላዊ ግዛቷ ግድብ ለምን ገነባች ከሚል ተቃውሞ የተነሳው የግብጽ ጥላቻ፥ ጦር ወደ ድንበራችን ማስጠጋትና ይህንንም ከአፍሪካ ህብረት ሶማሊያ ተልዕኮ ጋር ለማገናኘት መሞከሯ የድፍረት ድፍረት ሆኗል፡፡
ታሪካዊ ጠላታችን የሆነችው የግብጽ ሌላው ስውር ደባ ፖለቲካዊ ሲሆን ይህም ሀገራችን ሠላምና መረጋጋት እንዳታገኝ ማድረግ ነው፡ ፡ ውስጣዊና ውጫዊ ጠላቶቻችንን አይዞአችሁ እያለች ትጥቅና ስንቅ በማቀበል ለእኩይ ዓላማ ያነሳሳች ሲሆን በዚህም ግጭቶችና ውድመቶች እንዲቀሰቀሱ አድርጋለች፡፡
በሁሉም መስክ አሉታዊ የሆነው የግብጽ ድርጊት ሰሞኑን ተመልሶ ሲመጣ ልብ ያሉት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ሀገራችን ለህልውናዋ አስፈላጊ በሆነው የባህር በር ጉዳይ ጥያቄ በማንሳት የመጀመሪያ አሰናካይ ድንጋይ የወረወረችው ሀገር አሁን ኃይሏን አጠናክራ በጐረቤት ሃገር በኩል እስከ ድንበራችን ተጠግታለች፡፡
እነሱ አቅደው የመጡትን ያህል እኛም ሀገራችንን ለመከላከል ዕቅድ ማዘጋጀት ያስፈልገናል፡፡ በዓለም አቀፍ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ግንኙነት ውስጥ ጦር ወደ ሌላው ሀገር ማስጠጋት ጠብ ጫሪነት በመሆኑ እያወቁ ለመጡት ለሌላ ጊዜም ሙከራ እንዳያደርጉ ትምህርት መስጠትም የሚያስፈልግ ይሆናል ማለት ነው፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ብጥብጥና ውድመት በሀገራችን እንዲፈጠር ካደረገች በኋላ ከተቀሰቀሰው ጦርነት በስተጀርባ በመሆን ከሱዳን ጋር በመሆን ወረራ ለመፈጸምና መሬትንም ለመቁረስ ተንደርድራ ነበር፡፡
ነገር ግን፤ ውድ ኢትዮጵያዊያን በከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት ዕቅዷ ከሽፏል፡፡ በሱዳን ያጋጠመውን ችግርና በራሷ የደረሰውን ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ድቀት እያሰበች እስከአሁን ከእንቅስቃሴ ታቅባ ሰሞኑን ግን ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት መፈጸሟ ያሳፍራል፡፡
ከሀገራችን ጋር ፊት ለፊት መግጠም የማትፈልገው ሀገር ዛሬ ላይ ግን ወደ አፍንጫ የተቃረበች ይመስላል፡፡ እንቅፋቶችን ወደ ዕድል እየቀየረ የሚሠራው መንግሥትም አጋጣሚውን ወደ መልካም ዕድል የሚቀይርበት ጊዜ ይሆናል፤ ምክንያቱም ትልቅ ፖለቲካዊና ወታደራዊ አንድምታ ስላለው፡፡
በአካባቢው ካለው የኃይል አሰላለፍ ስንነሳ የሀገራችን መከላከያ ሠራዊት ሲያካሂድ ከነበረው የጸረ-አልሻባብ ዘመቻ ወጥቶ በድንበር ላይ እንዲሠፍር መደረጉ ትልቅ የስትራቴጂ ጠቀሜታ አለው፡፡ መልክአ ምድሩም የተሻለና ለእንቅስቃሴ አመቺ ይሆንለታል ማለት ነው፡፡
ለወታደራዊ እንቅስቃሴ ሌላው አመቺ አጋጣሚ የጠላት ኃይል ከአካባቢው መልክዓ- ምድር ጋር ያለመተዋወቁ ችግርን ተጋፍጦ የማለፍ አቅሙን ደካማ ያደርገዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ በሌሎች አፍሪካዊ ተልዕኮዎች የነበረው ደካማ አፈጻጸምም ዕድሉን የሚከለክለው ይሆናል፡፡
ከስትራቴጂያዊ ጉዳዮች አንጻር ስንመለከተው፥ ከአልሻባብና ሌሎች አረብ ሀገራት ጋር ሊፈጥሩት የሚችሉበት መስተጋብር ተጠቃሽ ሲሆን በተለይ ሁል ጊዜ አጋር አድርጋ ከምትመለከታቸው ሳውዲ ዓረቢያና ሌሎች ሀገራት የምታገኘው ድጋፍ ሥነ-ልቦናዋን ሊጠብቅላት ይችላል፡፡
እስከአሁን ግልጽ ያልሆነውን የአልሻባብ አቋም ከወሰድንም የሀገራችን መከላከያ ሠራዊት በወጣበት ማግሥት የግብጽ ጦር በመግባቱ ጥቃቱን እንደሚቀንስ ማረጋገጫ የለም፡፡ ግብጽም ከአሜሪካና ሌሎች ኃይላት ጋር ያላት ጥብቅ ወዳጅነት ቅራኔውን የሚያባብስባት ሊሆን ይችላል፡፡ የሃገሪቱ የተለያዩ ግዛት ነዋሪዎች ከኢትዮጵያ ጐን መቆም ሌላው ሃገራችንን የሚጠቅም ጉዳይ ነው፡፡
በአፍሪካ ቀንድ ለረጅም ዓመታት ሽብር ሲፈጥር የቆየው ይህ ቡድን፥ ከሶማሌ መንግሥት ጋር ለመስማማት የሚፈልግም አይደለም፤ ምክንያቱም እስከአሁን መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ አፍሪካ ህብረትና ከሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት የገንዘብ ድጋፎችን በመጠቀም ጉዳት ሲያደርስበት የቆየ ከመሆኑ አንጻር፡፡
በእነዚህ ምክንያቶች አሸባሪ ቡድኑ ግብጾች በመግባታቸው መነሻ ድርጊቱን የማያቋርጥ ከሆነ የሀገራችን መከላከያ ሳያስፈልግ አልሻባብ እራሱ ግብጾችን በማንበርከክ አላማቸውን ማክሸፍ ይችላል ማለት ነው፤ ያላቸውን ደካማ ወታደራዊ ብቃት ሁሉ በመጠቀም፡፡
የግብጽ ጣልቃ ገብነት ሌላው እንቅፋት ፖለቲካዊ ስህተቷ ሲሆን ይህ የሶማሊያን ሠላም ለማስከበር ደፋ ቀና ሲሉ ከነበሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ማለትም ከአፍሪካ ህብረት እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መርሆዎች ጋርም እንድትጋጭ ያደርጋታል፡፡ የሠላም አስከባሪው በወጣበት ቀጥተኛ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት መፈጸም ስለማትችል፡፡
ብዙ የውጭ መገናኛ ብዙሀን እንደሚያስቀምጡት ህግና ሥርዓት ማስፈን እንጂ ውጥረት እንዳይፈጠር ሀገራችን ለእነዚህ አካላት ይፋዊ አቤቱታ ማቅረብም ሊጠበቅባት ይችላል፡፡
More Stories
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ 120 የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ