የኢፌዲሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ከ82 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ መቆርቆር ቀበሌ ያስገነባው የንጹህ መጠ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

የኢፌዲሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ከ82 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ መቆርቆር ቀበሌ ያስገነባው የንጹህ መጠ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

ይህ ፕሮጀክት 13 ሺህ የአካባቢው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተገልጿል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢፌዲሪ ውሃ እና ኢነርጂ ሚስቴር ሚኒስትር ዴኤታና የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር አስፋው ዲንጋሞ፤ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማሻሻልና የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሀገር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የተመረቀው የውሃ ፕሮጀክት ብልጽግና ፓርቲ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመጨረስ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

በክልሉ በአጠቃላይ 7 ቢሊዮን ብር በመመደብ የህብረተሰቡን የንጽህ መጠጥ ውሃ ችግር የሚቀርፉ የውሃ ፕሮጀክቶች በመሰራት ላይ የሚገኙ ሲሆን አንዳንዶቹ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት በማድረግ ቀሪዎቹም በቀጣይ እንደሚመረቁ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ሀይሉ በበኩላቸው፤ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር መፍታት የትምህርት፣ የጤና የግብርና፣ የእናቶችና ህጻናትን ችግር መፍታት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የመቆርቆር የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ መጠናቀቅ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር የታየበት መሆኑንም አቶ ዳዊት አመላክተዋል።

ፕሮጀክቱ በምስራቅ አፍሪካ የበጀት ምንጭና በዞንና ወረዳ መንግስት የማቺንግ ፈንድ ግንባታው ተጠናቆ ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጥ ክፍት መደረጉን ኃላፊው ጠቁመዋል።

ከ82 ሚሊዮን 6 መቶ ሺህ ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የህ ፕሮጀክት 13 ሺህ የአካባቢው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አቶ ዳዊት አስረድተዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ውሃ ለሰው ልጅ መሰረታዊ ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን በአካባቢው የነበረውን የውሃ ችግር በመረዳት ዘላቂ እልባት ለመስጠት የመቆርቆር የውሃ ፕሮጀክት በልዩ ትኩረት በመስራት በአጭር ጊዜ ለምርቃት መብቃቱን ተናግረዋል።

ይህም ለሌሎች አካባቢዎች አርዓያነት ያለው ተግባር መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

የምሁር አክሊል ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብስራት ገብሩ፤ የተመረቀው የውሃ ፕሮጀክት ለዘመናት በውሃ እጦት ምክንያት ሲንገላቱ ለነበሩት ለመቆርቆር ቀበሌ ነዋሪዎች እፎይታን የፈጠረ ነው ብለዋል።

በተለዩያ የልማት ስራዎች ውስጣዊ የእንችላለን ስሜትን በማዳበር በትብብር መሰራት የህብረተሰቡን ችግር ለመቅረፍ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል።

በስፍራው አግኝተን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት በአካባቢው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊና ለጤና ችግሮች ሲዳረጉ እንደነበር ገልጸው አሁን ግን የመቆርቆር የውሃ ፕሮጀከት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት በመደረጉ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም የውሃ መስመሮች ከብልሽት መጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ለፕሮጀክቱ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና የሥራ ተቋራጮች እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ዘጋቢ፡ አስቻለው አማረ – ከወልቂጤ ጣቢያችን