አረፋ የሃጅ ስርአት የሚከወንበት ተራራማ ስፍራ ነው።
እንደ እምነቱ አስተምዕሮ የአረፋት ተራራ አላህ(ፈጣሪ) አደም እና ሐዋን ከጀነት ካስወጣቸው በኋላ ተበታትነው ከነበሩበት ዳግም የተገናኙበት ቦታ ነው ።
ለዚያም ነው በየአመቱ የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን በድምቀት የሚያከብሩት።
አረፋ ከእስልምና መሰረቶች መካከል የሀጅ ስርአት የሚፈፀምበት ነው።
ኢደ አል አድሃ /አረፋ በዓል ያለው ለሌለው የማካፈል ግዴታ እንዳለበት የሚያስቀምጠው ኡዱሂያ ወይንም የእርድ ስርዓት የበዓሉ አንዱ አካል ነው ።
የእርድ ስርዓት በሚከወንበት ወቅት ለእርድ የሚቀርበው እንሰሳ ሙሉ የሆነ ጤነኛ አካል ይዞ መቅረብ መሰረታዊ ነገር ነው።
ምህረት ለመጠየቅ ከእርድ ወይንም ከበዓሉ በፊት ባሉ አስርት የዙልሂጃ ቀናት ውስጥ ጥፍር አይቆረጥም ፤ፀጉር አይላጭም በአጠቃላይ ከአካል ምንም አይጎድልም፤ ምክንያቱም ለመላ አካላችን ምህረት ለመጠየቅ ስለሚከናወን።
ከዚህም መነሻ ለኡዱሂያ ወይንም ለእርድ የሚቀርበው ፍየል፣ በግ፣ግመልም ሆነ በሬ ሙሉ አካል ያለው መሆን አለበት።
ሥርዓቱን ፈጻሚ ወይንም አራጁ እንስሳውን በቤቱ አርብቶ ወይንም አደልቦ ቢሰዋ ይመረጣል።
መስዋዕት ሆኖ ለእርድ የሚቀርበው እንስሳ ጨቅላ ያልሆነ፣ያላረጀ፣ያልከሳ፣ ጥርሱ ያልወለቀ፣ቀንዱ ያልተሰበረ፣ከእንከን የጸዳ መሆን አለበት፤ ከአንድ አመት በታች የሆነ ፍየል፣ የስድስት ወር በግ ቢሆን ተብሎ መስፈርትም አለው ።
ምክንያቱም ንጹህና የተወደደ መሆን ስላለበት ቢሰጠን ደስ የሚለን መስጠት እንዳለብን የሚያስረግጥልን ሃይማኖቱ የከሳ ፣የሚያነክስ አካሉ የጎደለ በፍጹም መቅረብ እንደሌለበት ያስቀምጣል ።
ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸውን እስማኤልን ለአላህ(ለፈጣሪ) ሰዋልኝ ባላቸው መሰረት ለመሰዋት በሚያዘጋጁበት ጊዜ ልባቸው ፈራ፤ ታድያ ልጃቸው እስማኤል “አባቴ እዝነት ይታይብሃል የፈጣሪን ትዕዛዝ ለመፈጸም አትፍራ” አላቸው ታዛዥነቱን በመግለጽ።
ነብዩ ኢብራሂም ለመሰዋት ሙሉ ዝግጅት ካደረጉ በኋላ መለአኩ ጅብሪል እጃቸውን ይዞ አስቆማቸው፤ በምትኩ የደለበ የሰባም በግ አምጥቶ ሰጣቸው ለልጃቸው እስማኤል መስዕዋት (ፊዳ) ተደረገለት።
ለፈጣሪ መታዘዝ ታየበት ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በሚታረድበት ወቅት ንጹውን መልካሙን ማቅረብ ተወደደ።
ነብዩ ሙሐመድ “መታሰቢያነቱ የነብዩ ኢብራሂም መታዘዝ ማሳያ ነው ሲሉ እርድ በምትፈጽሙበት ጊዜ በጥንቃቄና በስርዓት ይሁን ሲፈጸም ሶስት ቦታ በማድረግ ፣አንድ ሦስተኛውን ለምስኪኖች ፣አንድ ሶስተኛውን ለዘመድ ለጓደኛ ፣አንድ ሶስተኛውን ደግሞ ለራሳችሁ አድርጉ” ብለው አስቀምጠዋል።
የኡዱሂያ የእርድ ስርዓት ከጀመዓ ሰላት መልስ በጋራ በመሆን ይታረዳል ፤ከዚያ በፊት ከሆነ የስጋ እርድ ብቻ ሆኖ ይቀራል ይለናል አስተምሮው።
የኡዱሂያ ስርዓት በሚፈጸምበት ጊዜም አላሁ አክበር (ተክቢራ) እየተባለ የኢድ አል አድሃ ሰላት በጀመዓ ይሰገዳል ከስግደት መልስ እርድ ይፈፀማል /ይታረዳል።
በማረድ ለመሰዕዋት ያሰበ ሰው ከበዐሉ በፊት ባሉ10 ቀናት ( ዙልሂጃ) ከገባ በኋላ እራሱን ይጠብቃል ፣ከሰውነቱ ምንም ነገር አይቀነስም ፀጉር መላጨት፣ ጥፍር መቆረጥ አይፈቀድም፣ ሙሉ መሆን አለበት ምክንያቱም ደግሞ በፀጉር ልክ ሃጅር ስለሚያስገኝ እና ሙሉ ሆኖ መቅረብ ሙሉ ማቅረብን ስለሚያሳይ።
የኡዱሂያ የእርድ ስርዓት የሚፈጸምባቸው ሦስት ቀናት ያሉ ሲሆን (ኢያመተሂጅሪቅ)ፈካ ያሉ ብርሃናማ ቀናት ናቸው።
የደስታ ቀን የሆኑና የማይፆምባቸው ቀናት ሲሆኑ በእነዚያም ቀናት (ዚያራ) ዘመድ መጠየቅ፣አንድነት የበለጠ መተሳሰብ የሚበዛበት ደስታን በጋራ በማሳለፍ የሚከበርባቸው ድንቅ ቀናት ናቸው።
ሼህ አህመድ ሀሰን በሀላባ ዞን የዌራ ወረዳ ሸርያ ፍርድ ቤት ቃዲ እና የከተማ መጂሊስ ሰብሳቢ ።
አዘጋጅ :ኤደን ተረፈ ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የኢፌዲሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ከ82 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ መቆርቆር ቀበሌ ያስገነባው የንጹህ መጠ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
በቅርቡ በሚሰጠው የ6ኛ እና የ8ኛ ክልላዊ ፈተና ላይ ከ53 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለፈተና እንደሚቀርቡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀዲያ ዞን ትምህርት መመሪያ አስታወቀ
“የብልጽግና ጉዞአችንና የንግዱ ማህበረሰብ ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ክልላዊ የንግዱ ማሕበረሰብ ማጠቃለያ የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው