ሀዋሳ፡ ጳጉሜ 05/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) “ዛሬን ለነገ ትውልድ በተግባር አሳይተን በጎነትና መልካምነትን እንዲያምኑ እንተጋለን” በሚል መሪ ቃል የነገ ቀን በጎፋ ዞን በጽዳት ዘመቻ፣ በእግር ጉዞና በፓናል ውይይት ተከብሯል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቦጋለ ፈይሳ ትውልድን መልካምነትና በጎነትን በማስተማር በቅንነትና በታማኝነት ማገልገልን ፍቅርንና የጊዜ አጠቃቀምን ማውረስ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለነገ ትውልድ የአባቶችን ባህልና ዕሴት ማስተዋወቅ የህልውና ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ካሴች ኤሊያስ፤ የትውልድ ግንባታ ከከተሞች ዕድገት ጋር የሚመጣጠን መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ለነገ ትውልድ ዛሬ ትጋታችንን በተግባር በማሳየት በስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመፍጠር መዘጋጀት ይኖርብናል ብለዋል፡፡
የጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ወሰነ ከተሜነት የነገው ከተሞች ዕድገት፣ የትውልድ ቅብብሎሽ እና የመደመር ትውልድ ሚና በሚል ርዕስ ለፓናል ውይይት የተዘጋጀ ስነድ ባቀረቡበት ወቅት ጽዱና ንጹህ ከተማን ለትውልድ በማስተላለፍ በጎነትንና ፍቅርን ለትውልድ ማሻገር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የሳውላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እርቦላ እርኮ ዛሬ ላይ ሆነን ትውልድ ተሻጋሪ ተግባር መፈጸም አለብን ብለዋል።
ከተማችንን ውብና ጽዱ በማድረግ ለትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መትጋት አለበት ብለዋል።
ዞኑ የህፃናት ፓርላማ ምክትል አፈ ጉባኤ ህፃን አዶናይ አማኑኤል የነገውን ትውልድ ብሩህ ተስፋ የሚያሳይ ሥነ-ጹሑፍ አቅርባለች።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከተሞችን ማስዋብና ለኑሮ ምቹ ማድረግ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት በመሆኑ የበኩላቸውን አሻራ ለማስቀመጥ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቦጋለ ፈይሳ፣ የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ካሴች ኤሊያስን ጨምሮ የዞንና የሳውላ ከተማ አመራሮች፣ ነዋሪዎችና ህጻናት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ 120 የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ