ሀዋሳ፡ ጳጉሜ 04/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በቀጣዩ ሶስት ወራት ለወባ መራቢያ ምቹ ወራት በመሆናቸው የመከላከሉ ስራ ተጠናክሮ ሊሰራ እንደሚገባ የደቡብ ምእራብ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።
ክልል አቀፍ የወባ በሽታ መከላከልና ቁጥጥር ስራ ላይ ያተኮረ ውይይትና ባለፉት ሁለት ወራት በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራት የአፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ወይይት የተካሄደ ሲሆን፥ የመከላከልና የቁጥጥር ስራውን ለማጠናከር የአመራር ቁርጠኝነትን ወሳኝ ተግባር ለመሆኑ ተመላክቷል።
የወባ በሽታ ለመከላከል በተሰራው ስራ ውጤት መገኘቱን የሞት መጠኑም ከጊዜ ወደጊዜ መቀነሱን ነው በውይይቱ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች የተናገሩት።
በተለይም ለስርጭቱ መቀነስ ከክልል ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ተቀናጅቶ በመሰራቱ ለውጥ መገኘቱን የተናገሩት ተሳታፊዎቹ ቀሪ የሚሏቸውን ተግባራት በቀጣይ አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋልም ብለዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በበኩላቸው የወባ በሽታ ስርጭት ለክልሉ ህዝብ ፈታኝ እንደነበር ጠቁመው፥ የክልሉ መንግስት በወሰደው ቁርጠኛ አቋም የበሽታውን ስርጭት መቀነስ ተችሏል ብለዋል።
የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል ቅንጅታዊ ስራዎችን በማስቀጠል የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅድ በማዘጋጀት የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሞችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
የደቡብ ምእራብ ክልሉ ምክርቤት ዋና አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ በበኩላቸው የተጀመሩ የወባ በሽታ መከላከል ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል ።
በተለይም በህክምና ተቋማቱ ላይ የሚስተዋሉ ህገወጥ የመድኃኒት ዝውውርና ስርቆት ላይ የሚወሰደው የህግ የበላይነት ስርአት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ተጠያቂነት የማስፈን ስራ በተገቢው ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በበኩላቸው በክልሉ ለወባ በሽታ ስርጭት መቀነስ የሁሉም ባለድርሻ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፥ የተገኘው ውጤት ወደኋላ እንዳይቀለበስ በቀጣይነት አመራሩ ግንባር ቀደም ሚናውን ሊጫወት ይገባል ብለዋል።
የግንዛቤ ስራዎችን በማስቀጠል አስፈላጊውን ግብኣት እና በጀት በመመደብ ዞኖችና ወረዳዎች ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባቸውም አንስተዋል።
ቀጣይ ሶስት ወራት ለወባ ትንኝ መራባት አመቺ ጊዜ በመሆኑ ህብረተሰቡ ዉሃ ያቋሩ አካባቢዎች የማዳፈንና የማፋሰስ እንዲሁም የአጎበር አጠቃቀም ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባዉ አቶ አብራሂም የተናገሩትም ።
ከመረጃ አያያዝ ጋር የሚታዩ ጉድለቶችን የማጥራት ስራ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ኢብራሂም የግብአት ቁጥጥር ስረአቶችም በተጠናከረ መልኩ እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።
የደቡብ ምእራብ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪው አቶ ጸጋዬ ማሞ በበኩላቸው በክልሉ የወባ ስርጭት መስፋፋት ፈታኝ እንደነበር አውስተው በተቀናጀ ምሪት በተሰራው ስራ ውጤት የመጣ ቢሆንም፥ ውጤቱ በቂ ነው የሚያስብል ባለመሆኑ ቀጣይነት እንዲኖረው አመራሩ እቅድ በማቀድ በሳምንት አንድ ቀን የወባ ሳምንት በመምረጥ የመከላከል ስራውን አቀናጅቶ በተገቢው መምራት አለበት ብለዋል።
ዘጋቢ፡ አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ 120 የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ