የኅብር ቀን በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ “ኅብራችን ለአንድነታችንና ለዘላቂ ሰላማችን” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከበረ


“ኅብራችን ለሰላማችን” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ የኅብር ቀን እንዲከበር መወሰኑን ተከትሎ በዞኑም የሳውላ ከተማ ነዋሪዎች እና ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።

ዞኑ የጎፋና የኦይዳ ነባር ብሄረሰቦች እንዲሁም በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ እና የተለያዩ ቋንቋ፣ ባህል እና እሴት ያለው ህብረ ብሔራዊ ዞን ነው ያሉት የጎፋ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ታደለ ያዕቆብ ዕለቱ በኅብር ውስጥ የሚገኘውን አቅምና አንድነት የምናሳይበት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች ተቻችለው፣ ተዋደውና ተከባብረው ያለልዩነት የሚኖሩባት ኅብረ ብሔራዊት ሀገር መሆኑዋን ተናግረዋል።

በኅብር ውስጥ አልበገርም ባይነት፣ አሸናፊነትና ጀግንነት መኖሩንም አቶ ታደለ አስገንዝበዋል።

የዞኑ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ካሳሁን አባይነህ በበኩላቸው ኅብር እኛ ኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክ፣ የውብና ደማቅ ባህል ባለቤት መሆናችንን የምናሳይበት ቀን ነው ብለዋል።

የትላንት ድላችን፣ የዛሬ ጥንካሬያችን የነገ ተስፋችን ሚስጥር ኅብር ነው ብለዋል።

እንደሀገር የኅብር ቀን “ኅብር የትናንትም የዛሬም የነገም ስኬት ሚስጥራችን፣ “ኅብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት”፣ “ኅብራችን ተፈጥሮአዊ ፀጋችን ነው”፣ ኅብራችን ውበታችን ነው” በሚሉ መልዕክቶች ተከብሯል።

ያነጋገርናቸው የበዓሉ ተሳታፊዎች በበኩላቸው አንድነታችንን በማጠናከር ለዞኑ ሰላምና ሁለንተናዊ ዕድገት በጋራ ተቀናጅተን መስራት ይገባል ብለዋል።

የከተማው ነዋሪዎች እና ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በተገኙበት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ ባህላዊ ውዝዋዜዎች እና በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን