በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሉዓላዊነት ቀን “ኅብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ቃል በወልቂጤ ከተማ በልዩ ልዩ ሁነቶች ተከብሯል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ መነቴ ሙንዲኖ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ሀገራችን የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት ከሆኑ የአፍሪካ ሀገራት መካከል ግንባር ቀደም መሆኗን ተናግረው ለዚህም ስኬታማነት በየአካባቢው ያሉ የታሪክ አሻራዎች አብነት መሆናቸውን አንስተዋል።
እነዚህ የማንነታችን ምልክት የሆኑ የታሪክ አሻራዎች እስከዛሬ ድረስ ሊቆዩ የቻሉት በጥንት አባቶቻችን ብርቱ ጥረትና ከብረት በጠነከረ አንድነታቸው መሆኑን በማውሳት ሀገራችንን በቅኝ ግዛት ለማንበርከክ ጠላቶቿ በተለያዩ ጊዜያት ሉአላዊነቷን በሀይል በመዳፈር ወረራ መፈጸማቸውን ገልፀዋል።
በዚህም አይበገሬዎቹ አባቶቻችን የጠላቶቻችንን ወረራ አሳፍረው መመለሳቸውን በመጥቀስ፤ ስለሆነም አዲሱ ትውልድ ጀግኖች አባቶቻችን በክብር ያቆዩልንን ሀገር የመጠበቅ ሀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ምክትል አፈ ጉባኤዋ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ነጻነቷን ጠብቃ ባንዲራዋን ከፍ አድርጋ እያውለበለበች ያለች ኩሩ ሀገር መሆኗን ያመላከቱት ምክትል አፈ ጉባኤዋ መተኪያ የሌላትን ህይወታቸውን በመገበር በደም እና በአጥንታቸው የሀገራችን ሉአላዊነት ተጠብቆ እንዲቆይ ላደረጉ ጀግኖች ምስጋና አቅርበዋል።
በሀገሪቱ የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆን የውስጥ ሰላማችንን መጠበቅ ዋነኛ ጉዳይ መሆኑን በመጠቆም ልዩነቶችን በዲሞክራሲያዊ መንገድ በውይይት የመፍታት ባህል ማዳበር ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በዛሬው ዕለት የተከበረው የሉዓላዊነት ቀን በዓል ለሀገራችን ክብር፣ እድገት እና ብልጽግና አሻራቸውን አኑረው ያለፉትን ጀግኖች የምናስብበት ነው ያሉ ሲሆን ሁሉም ለሀገሪቱ ዘብ በመቆም ለዕድገትና ብልፅግናዋ ሌት ተቀን መትጋት እንዳለበት ነው ወ/ሮ መነቴ የተናገሩት።
የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ኢያሱ ሻንቆ በበኩላቸው ሉአላዊነታችንን በላባችን የማናጸና ከሆነ ሉኣላዊነታችን የተሟላ ሊሆን እንደማይችል አስረድተዋል። በመሆኑም የሉአላዊነታችን ዋስትና አንድነታችን በመሆኑ ለውጤታማነቱ ዘመኑን የሚመጥን ሁሉን አቀፍ ስራ መሥራት አለብን ብለዋል።
የመወያያ ፅሁፍ ያቀረቡት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪው ታኖ ገትር ኢትዮጵያ በታሪኳ የምትታወቅና በተለያዩ ጊዜያት ወራሪዎቿን አሳፍራ በመመለስ አይበገሬነቷን ለዓለም ያስመሰከረች ሀገር መሆኗን በማመላከት ሀገሪቱ በአድዋ ጦርነነት ወቅት ያስመዘገበችውን ድል በማሳያነት አንስተዋል።
የዝግጅቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም ሀገሪቱ የቆየችው በየደረጃው በተከፈለ ዋጋ መሆኑን ጠቁመው ህዝቡ በሀገሩ ሉአላዊነት ጉዳይ እንደማይደራደር ገልፀዋል።
በመሆኑም የውስጥና ሀገራዊ የጸጥታ ችግሮች ጥሪ በሚቀርብበት ወቀት በቅንጅት መፍታት ያለበት የፀጥታ ሀይሉ መሆኑን ጠቁመው የፀጥታ ሀይሉ ተግባሩን ሲፈጽም እንደሀገር ከፍ ብሎ ማሰብ እንዳለበት ተናግረዋል።
ሌብነትን ለማስቀረት ተግቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ የገለፁት ተሳታፊዎቹ በየደረጃው የሚስተዋሉ የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመርሃግብሩ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቢሮ ሀላፊዎች፣ ሰራተኞች፣ የጉራጌ ዞንና የቀቤና ልዩ ወረዳ አመራሮችና በክብር የተመለሱ የሰራዊት አባላት እንዲሁም የፖሊስ አባላት ታድመዋል።
ዘጋቢ፡ መሃመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የሚባክነውን የህዝብና የመንግሥት ሀብት ማዳን መቻሉ ተገለጸ
ቅንጅታዊ አሠራርን በማስፈን ጥምር ደን መጠበቅ፣ ማስፋትና መጠቀም እንደሚገባ ተጠቆመ
የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በማዘመን የዘርፉን ውጤታማነት ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ