ልማት ማህበሩ ከመንግስት ጎን በመሆን የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ማህበሩ ባለፉት ስድስት ወራት ገንብቶ ያጠናቀቀውን የወናጎ ወረዳ ባንቆ ኦኮቶ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዛሬው ዕለት አስመርቋል፡፡
ትምህርት ቤቱን ገንብቶ ለመጨረስ ስድስት ወራት ብቻ መፍጀቱን የገለጹት የጌዴኦ ልማት ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ብዙነህ ንጉሴ ግንባታውም ከ13.6 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የወጣበት ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡
የጌዴኦ ልማት ማህበር ምክትል ቦርድ ሰብሳቢና የዲላ ዩኒቨርሲት መምህር እና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋኖ በቀለ በበኩላቸው ማህበሩ ምንም እንኳን በራሱ የሚያመነጨው የገቢ አማራጮች የሌሉት ቢሆንም ከህብረተሰቡ የሚሰበሰበውን ውስን ሀብት በአግባቡና በጥንቃቄ በመጠቀም መንግስት መሸፈን ያልቻለውን የህብረተሰብ አንገብጋቢ ችግር በመለየት መፍትሔ እየሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳደር ዶ/ር ዝናቡ ወልዴ እንደሀገር የመሻገር ቀን እየተከበረ ባለበት ወቅት የተመረቀው ይህ ፕሮጀክት ከትምህርት ስብራት ችግር ተሻግረን የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ወደማፍራት ምዕራፍ መሸጋገራችንን ያረጋገጥንበት ዕለት በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
አክለውም ልማት ማህበሩ በቀጣይ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርናና ሌሎች መስኮች ለመስራት የወጠናቸውን ዕቅዶች ከዳር እንዲያደርስ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበው ዞኑም በሙሉ አቅሙ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
ዘጋቢ: ሳሙኤል በቀለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶችን የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ለመቅረፍ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጎልበት የጤና አደረጃጀቶችን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ
ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመግባት ዕድል ያገኙ ተማሪዎች የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ትምህርታቸው ላይ ብቻ ሊያተኩሩ እንደሚገባ መልዕክት ተላለፈ
የሀዲያ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ለ2018 በጀት ዓመት ከ10 ቢልዮን ብር በላይ በጀት ለተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲውል በተገቢው እንደሚሠራ ገለፀ